ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም እያደረገች ያለው ጥረት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም እያደረገች ያለው ጥረት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነው

ጂንካ፤ መስከረም 3/2018 (ኢዜአ)ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመቋቋም ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እያደረገች ያለው ጥረት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉ በኢጋድ የክፍለ-አህጉሩ ዳይሬክተር ሙባረክ ማቦያ ገለፁ።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) አባል አገራት ተወካዮች በኢጋድ መሪነት በኢትዮጵያ ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች እየተተገበሩ ያሉ ፕሮጀክቶች አፈፃፀምን ተመልክተዋል።
ልዑካኑ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን በና-ፀማይ ወረዳ ድርቅን ለመቋቋም በሚደረገው ሂደት በአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ዘንድ የመጡ ተጨባጭ ለውጦችንም መመልከት ችለዋል።
በኢጋድ የክፍለ አህጉሩ ዳይሬክተር ሙባረክ ማቦያ እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመቋቋም ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እያደረገች ያለው ጥረት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነው።
በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ፣ ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች በመስኖ ልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶች ውጤት እያስመዘገቡ እንደሆነ መመልከታቸውን ተናግረዋል።
እንዲሁም የአርብቶ አደሩን የኢኮኖሚ አቅም ለማሳደግ፣ የእንስሳት ምርታማነትን ለማሻሻል፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋንን ለማሳደግና ድርቅን የሚቋቋም ማህበረሰብ ለመፍጠር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል።
በሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በዝርዝር አቅርበው እንደነበር ያስታወሱት ዳይሬክተሩ በኢትዮጵያ ያደረግነው ምልከታም ይህንኑ በተግባር የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የድርቅ መቋቋም እና የአርብቶ አደር ኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራም ብሔራዊ አስተባባሪ ጀማል አልዬ፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመቋቋም የተሻለ ውጤት ማምጣቷን ገልጸዋል።
የኢጋድ አባል አገራት በኢትዮጵያ እያደረጉ ያሉት ጉብኝትም ያለውን ልምድና ተሞክሮ ለመቅሰምና በሌሎች የድርጅቱ አባል ሀገራትም ተሞክሮውን ለማስፋት ታስቦ የተደረገ እንደሆነም አስረድተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤካል ነትር በበኩላቸው፤ በክልሉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የአርብቶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ መሆኑን አንስተዋል።
በቀጣይም የእንስሳት ጤናን በመጠበቅ፣ ድርቅን አስቀድሞ በመከላከል፣ አርብቶ አደሩን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖ የማይበገር ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ የአደጋ ስጋት ቅነሳና አካታች የኢኮኖሚ እሴት ማሻሻያ ፕሮጀክት አስተባባሪ ስዩም መታፈሪያ (ዶ/ር) ባደረጉት ገለፃ የደቡብ ኦሞ ዞን ዝናብ አጠርና በተደጋጋሚ ለድርቅ ተጋላጭ የሆነ አካባቢ እንደነበር ገልጸው ተጋላጭነቱን ለመቀነስ በተከናወኑ ዘርፈ-ብዙ ተግባራት ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ገልፀዋል።
ቡድኑ በደቡብ ኦሞ ዞን በና ፀማይ ወረዳ ለመስኖ፣ ለሰውና ለእንስሳት ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጠውና 300 ሜትር ጥልቀት ያለው እንዲሁም በፀሐይ ኃይል በሰከንድ 26 ሊትር ውሃ የሚያመነጨውን ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ፕሮጀክትንም ተመልክቷል።
ከዚህ በተጨማሪ የእንስሳት ማቆያ እና የእንስሳት የገበያ ማዕከል፣ የከብቶች የመኖ ልማት እና የመኖ ማከማቻ መጋዘንና ሌሎች ፕሮጀክቶችንም ጎብኝተዋል።
ልዑካን ቡድኑ በአፋርና በሶማሌ ክልል ምልከታ ያደረጉ ሲሆን ከደቡብ ኢትዮጵያ በመቀጠል ወደ ኦሮሚያ ክልል በማቅናት በቦረና ዞን ምልከታ እንደሚያደርጉም ተመላክቷል።