ከበደ ባልቻ፤ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ሜዳሊያ ያስገኘው ታሪካዊ አትሌት - ኢዜአ አማርኛ
ከበደ ባልቻ፤ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ሜዳሊያ ያስገኘው ታሪካዊ አትሌት
የመጀመሪያው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተካሄደው እ.አ.አ 1983 በፊንላንድ ሄልሲንኪ ነበር።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው የመጀመሪያ ተሳትፎዋ በወንዶች 5000 ሜትር ፣ 3000 ሜትር መሰናክል፣10000 ሜትር ፣ ማራቶን እና 20 ኪሎ ሜትር ርምጃ ተካፍላለች።
በወንዶች ማራቶን የተደረገው ውድድር ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ሜዳሊያ ያገኝበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነበር።
በውድድሩ ላይ የተሳተፈው ኢትዮጵያዊ አትሌት ከበደ ባልቻ 2 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ከ27 ሴኮንድ አውስትራሊያዊውን አትሌት ሮበርት ዲ ካስቴላን ተከትሎ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ አገኝቷል።
ከበደ በወቅቱ ያስገኘው ብቸኛ የብር ሜዳልያ ኢትዮጵያ በሜዳልያ ደረጃ ሰንጠረዥ ዝርዝር ላይ እንድትሰፍርና ከኩባ፣ኔዘርላንድ፣ ሮማኒያ እና ስፔን እኩል የ 15ኛነት ደረጃ ይዛ እንድታጠናቅቅ ማስቻሉን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል።
አትሌት ከበደ ባልቻ እ.ኤ.አ በ1979 በሴኔጋል ዳካር በተካሄደው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የማራቶን የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ፣ እ.አ.አ በ1985 በግብጽ ካይሮ በተካሄደው የአፍሪካ ሻምፒዮና በማራቶን የብር ሜዳልያ አሸናፊ፣ እ.ኤ.አ በ 1987 በኬንያ ናይሮቢ በተከናወነው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በማራቶን የነሐስ ሜዳልያ ባለቤት የነበረ ሲሆን በወቅቱ ባጋጠመው የጤና እክል ሳይበገር የሜዳልያ ባለቤት መሆን ችሏል፡፡
እ.ኤ.አ በ1980 በቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት (በአሁኗ ሩሲያ) በተከናወነው የኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክለው ከቀረቡት ሶስት አትሌቶችም አንዱ ነበር፡፡
ለ18 ዓመታት ኑሮውን በካናዳ አድርጎ የቆየው የቀድሞው ብርቱ አትሌት ከበደ ባልቻ ባጋጠመው የጤና እክል የህክምና እርዳታ ሲደረግለት ቆይቶ ሐምሌ 3 ቀን 2010 ዓ.ም በ67 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን የፌዴሬሽኑ መረጃ ያሳያል።
ከበደ ባልቻ ዛሬ በህይወት ባይኖርም በሂልሲንኪ ጎዳናዎች ላይ ሀገሩን ወክሎ በማራቶን የብር ሜዳልያ በማስመዝገብ የሰራው ገድል በወቅቱ የሀገሩን ሰንደቅ ከፍ ያደረገ እንዲሁም በታሪክ መዛግብት ላይ ሰፍሮ እስከ አሁን የዘለቀ ወደፊትም የሚኖር ህያው ታሪኩ ነው።