በሶማሌ ክልል የመጣውን ለውጥና የተመዘገበውን ስኬት የሚገልጥ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ስራ ለማከናወን ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል የመጣውን ለውጥና የተመዘገበውን ስኬት የሚገልጥ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ስራ ለማከናወን ጥረት እየተደረገ ነው

ጅግጅጋ ፤ መስከረም 2/2018 (ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል የመጣውን ለውጥና የተመዘገበውን ስኬት የሚገልጥ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ስራ ለማከናወን ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ ለሚገኙ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን አመራሮችና ባለሙያዎች የድህረ እውነት ዘመን የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሚና እና አስተዋጽኦ በተመለከተ ስልጠና ተሰጥቷል።
በስልጠናው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ምክትል ቢሮ ሃላፊ በሺር ሼኽ ሰኢድ፤ በፈጣኑ የዲጂታል ዓለም ጠንካራና ከዘመኑ ጋር የሚራመድ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ስራ ያስፈልጋል ብለዋል።
ለዚህም የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች የላቀ ዝግጁነት የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ከዲጂታሉ ዓለም ፍጥነት ጋር በመራመድ ትክክለኛ መረጃዎችን በፍጥነት ማጋራትና ሀሰተኛ መረጃዎችን ማጋለጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በሶማሌ ክልል ባለፉት የለውጥ ዓመታት በርካታ አስደናቂ ስኬቶች መመዝገባቸውን አንስተው ከመጣው ውጤት አንፃር ሰፊ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ስራ ይጠይቃል ብለዋል።
በክልሉ ከተመዘገበው ውጤት አንፃር በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ እስካሁን የተሰራው ስራ በቂ ባለመሆኑ የመጣውን ለውጥና የተመዘገበውን ስኬት የሚገልጥ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ስራ ለማከናወን ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ የመንግሥት መረጃ አስተዳደር እና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብድረዛቅ ካፊ፤ የክልሉን ሰላም በማጽናትና የልማት ስራዎችን በማጠናከር ረገድ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ብዙ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል ሲሉ ተናግረዋል።
ከክልሉም ባለፈ ሀገርን በሚመለከት የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማጋለጥ ፈጣን፣ እውነተኛና ትክክለኛ መረጃዎችን ማድረስ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ የጋራ የልማት አጀንዳ፣ ዘላቂ ሰላምና ብልፅግናን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ሰፊ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልፀው ህብረ ብሔራዊ አንድነትና የጋራ ትርክት በመገንባት ረገድ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ይበልጥ ተቀራርቦና ተቀናጅቶ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።