ቀጥታ፡

በባሌ ዞን ከ800 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

ሮቤ፤ መስከረም 2/2018 (ኢዜአ)፦ በባሌ ዞን ከ800 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስና የደንብ ልብስ ድጋፍ ተደረገ፡፡ 

ድጋፉን ያደረጉት በኦሮሚያ ልማት ማህበር የባሌ ቅርንጫፍና በኢትዮ ቴሌኮም የደቡብ ደቡብ ምሥራቅ ሪጅን ጽህፈት ቤት መሆናቸውም ተመልክቷል። 


 

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሻለ ዲሳሳ፤ የተደረገው ድጋፍ በትምህርት ቁሳቁስ ምክንያት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ለመግባት ችግር እንዳይገጥማቸው የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ከዚህ በፊት በዞኑ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 60 ሺህ ለሚሆኑ የአቅመ ደካማ ቤተሰብ ተማሪዎች የትምህርት መርጃ ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉን አስታውሰው በተጨማሪም ኢትዮ ቴሌኮም እና የኦሮሚያ ልማት ማህበር ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል። 

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አልይ በበኩላቸው በዞኑ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሁሉም ህፃናት መደበኛ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። 


 

የኦሮሚያ ልማት ማህበር የባሌ ቅርንጫፍና ኢትዮ- ቴሌኮም የደቡብ ደቡብ ምሥራቅ ሪጅን ያደረጉት ድጋፍ ለሌሎች ተቋማትም ተሞክሮ የሚሆን ነው ብለዋል። 

የኦሮሚያ ልማት ማህበር የባሌ ቅርንጫፍ አስተባባሪ አቶ ማስረሻ ቶላ፤ ማህበሩ በተለያዩ መስኮች ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን አስታውሰው ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉም የዚሁ አካል ነው ብለዋል።


 

በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንዳይርቁ ለማድረግ የበኩሉን ጥረት ማድረጉን አንስተው በቀጣይም አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል። 

የደቡብ ደቡብ ምሥራቅ ሪጅን ተወካይ አቶ መሐመድ ሁሴን አብደላ፤ ኩባንያው የቴሌኮም አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ በማህበረሰባዊ አገልግሎት ድጋፍና ትብብር የሚያደርግ መሆኑን አንስተዋል።


 

በዚህም መሰረት በዛሬው እለት ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

ከድጋፉ ተጠቃሚ ተማሪዎች መካከል ተማሪ ሱመያ ሙአዝ፥ ተቋማቱ ላደረጉላት እገዛና ድጋፍ ምስጋናዋን አቅርባለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም