ቀጥታ፡

በጉራጌ ዞን የተገነባው አማርድ 2ኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታው ተጠናቆ ተማሪዎችን እየተቀበለ ነው

ወልቂጤ ፤መስከረም 2/2018 (ኢዜአ)፡- በጉራጌ ዞን የተገነባው አማርድ 2ኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታው ተጠናቆ ተማሪዎችን እየተቀበለ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

በዞኑ አዲስ የተገነባው አዳሪ ትምህርት ቤት የላቀ ውጤት ያላቸውን ተማሪዎች በማወዳደር በመቀበል ላይ ሲሆን በተያዘው ዓመት የመማር ማስተማር ስራውን ይጀምራል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ፤ በ2018 ዓ.ም የአዳሪ ትምህርት ቤቱ ስራ መጀመር ትልቅ ስኬት መሆኑን አንስተው በዞኑ ትምህርትን የማስፋትና ጥራትን የማስጠበቅ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።


 

የአዳሪ ትምህርት ቤት በማቋቋም ከራሳቸው ተርፈው የሃገሪቱን ራዕይ ለማሳካት የሚችሉ በእውቀታቸው እና በስነ ምግባራቸው ምስጉን የሆኑ ተማሪዎችን ለማስተማር ጥረት ሲደረግ ቆይቷል ብለዋል። 

መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረትም የአዳሪ ትምህርት ቤቱ ግንባታ በ2013 ዓ/ም ተጀምሮ አሁን ላይ በማጠናቀቅ በተያዘው የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን እየተቀበለ ይገኛል ብለዋል።

የአማርድ 2ኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት ዘመናዊ የመማሪያ ክፍሎችን ጨምሮ፣ ቤተ ሙከራ፣ ቤተ-መፃህፍት፣ የተማሪዎች ማደሪያና መመግቢያ ክፍሎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችና ሌሎች 19 ዓይነት ግብዓትን የያዘ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል ። 


 

ተማሪዎች ለትምህርት የሚያስፈልጉ ግብዓት ተሟልቶላቸው ሙሉ ጊዜያቸውን ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ እንደሚደረግም አስረድተዋል። 

ለዚህም የመምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች ቅጥርን ጨምሮ ለትምህርት የሚያስፈልጉ የተማሪዎች ቀለብና የትምህርት ቁሳቁስ መሟላቱን አንስተዋል ።

 
 

ተማሪዎች ወደ አዳሪ ትምህርት ቤቱ ሲገቡ በስነ-ምግባራቸው የተመሰገኑና ከ6ኛ ክፍል ጀምሮ ያላቸው የትምህርት አቀባበል ታሪክን መሰረት በማድረግ እንደሆነ የገለፁት ደግሞ የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወልደ ማርያም ናቸው። 

ትምህርት ቤቱ ከ9ኛ እስከ 12ኛ  ክፍል ያሉ ተማሪዎችን እንደሚቀበል ገልፀው በዘቢዳር ልማት ኢንሼቲቭ፣ በዞኑ አስተዳደር እና በሌሎች አካላት ጋር የጋራ ትብብር እንደሚተዳደርም ጠቁመዋል።

አማርድ አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዘንድሮ 120 ተማሪዎችን እንደሚቀበል የተገለፀ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባር ሲገባ ደግሞ ከ1 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተናግድም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም