ቀጥታ፡

ክልሉ በተያዘው ዓመት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካትን ቀዳሚ አጀንዳ አድርጎ እየሰራ ነው

ባህርዳር ፤ መስከረም 2/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በተያዘው ዓመት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካትን ቀዳሚ አጀንዳ አድርጎ እየሰራ መሆኑን የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ሰላም እየተረጋጋ በመምጣቱ ተኪ ምርቶችን ከማምረት ጎን ለጎን ከ4 ሺህ 600 በላይ ባለሃብቶችን በአዲስ መልክ ወደ ክልሉ ለመሳብ ቢሮው ትኩረት መስጠቱም ተመላክቷል።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ ለኢዜአ እንደገለጹት ቢሮው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካትን ቀዳሚ አጀንዳ አድርጎ እየሰራ ነው።

በተለይም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ለኢኮኖሚው ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አንስተዋል።

ከተኪ ምርቶች ውስጥም ምግብና ምግብ ነክ፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ መድኃኒትና ማህበረሰቡ በየዕለቱ የሚጠቀምባቸው የተለያዩ ምርቶች እንደሚገኙበትም ጠቁመዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ የክልሉ መንግስት ሊያወጣ የሚችለውን ከ560 ነጥብ 97 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ለማዳን ግብ አስቀምጦ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ የወጪ ምርቶችን በብዛትና በጥራት አምርቶ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

ከዚህም ከ167 ነጥብ 17 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለሀገሪቷ ለማስገኘት ቢሮው ትኩረት ሰጥቶ የድጋፍና ክትትል ተግባሩን አጠናክሮ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ ሰላም እየተረጋጋ በመምጣቱም 4 ሺህ 600 የውጭና የሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮች በበጀት ዓመቱ ወደ ክልሉ መጥተው መዋዕለ ንዋያቸውን ፈሰስ በማድረግ ራሳቸውንና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አስታውቀዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ብርሃን ገብረህይወት በበኩላቸው በከተማ አስተዳደራቸው ከ60 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች ተኪ ምርትን በብዛትና በጥራት እያመረቱ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ከሰባት የሚበልጡ ኢንዱስትሪዎች ደግሞ በውጭ ምንዛሬ ገቢ የሚያስገኙ ምርቶችን በትኩረት እያመረቱ ነው ብለዋል።

በተለይም በቴክስታይልና ጋርመንት፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በኬሚካል፣ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች ዘርፍ የተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ተኪ ምርት በማምረት ረገድ ላቅ ያለ ሚና እንዳላቸውም አብራርተዋል። 

በተያዘው ዓመትም የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን ወደ ከተማዋ በመሳብ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የመተካቱ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም