ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለአፍሪካዊያን ትልቅ ኩራት እና መነሳሳትን የሚፈጥር ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለአፍሪካዊያን ትልቅ ኩራት እና መነሳሳትን የሚፈጥር ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 2/2018 (ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለአፍሪካዊያን ትልቅ ኩራት እና መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ተናገሩ፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ለቀጣናዊ ትስስር ያለው አበርክቶም የጎላ ስለመሆኑ አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቁመዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ባለፈዉ ሳምንት ጳጉሜን 4 ቀን 2017 በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ መመረቁ ይታወቃል፡፡
ግድቡ የኃይል አቅርቦትን በመጨመርና የኢኮኖሚ ዕድገትን በማፋጠን ረገድ ለኢትዮጵያ ህዝብ የአዲስ ዓመት በረከት ተደርጎም የሚወሰድ ነው፡፡
በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙ የጎረቤት ሀገራት መሪዎች ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መግዛት እንደሚፈልጉም ባደረጉት ንግግር አረጋግጠዋል፡፡
ይህም ግድቡ ከኢትዮጵያ የተሻገረ አፍሪካዊ በረከት መሆኑን በግልጽ ያሳየም ሆኗል፡፡
ከዓለም 10 ታላላቅ ግድቦች አንዱ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ በራስ አቅም መገንባቱ ለአፍሪካ ትልቅ ኩራት እና መነሳሳትን የፈጠረ ጉዳይ መሆኑንም የተለያዩ አፍሪካዋያን ተናግረዋል።
በኢንቴቤ አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የበረራ ተቆጣጣሪ የሆኑት ዛም ዛም ግድቡ ያለ አንዳች የውጭ ድጋፍ መገንባቱ የሚያኮራ ነው ብለዋል፡፡
በኬንያ አካባቢ፣ አየር ንብረት ለውጥ እና ደን ልማት ሚኒስቴር የአየር ንብረት ለውጥ ምክትል ዳይሬክተር ሚካኤል ኦኩሙ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ መንግስት እንደዚህ ዓይነት ግዙፍ እና አስደናቂ ግድብ መገንባቱ ትልቅ እንቅስቃሴ ነው ብለዋል፡፡
ግድቡ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካዊያን ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡
በኢንቴቤ አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የበረራ ተቆጣጣሪ ዛም ዛም ግድቡ ቀጣናዊ ትስስርን በማሳለጥ ረገድ ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወትም ገልጸዋል፡፡
ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚመነጨው ንጹህ ሃይል በመሆኑ በአህጉሪቱ ለሚደረገው አየር ንብረት ለውጥ ትግል ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡
በኬንያ የአካባቢ፣ አየር ንብረት ለውጥ እና ደን ልማት ሚኒስቴር የአየር ንብረት ለውጥ ምክትል ዳይሬክተር ሚካኤል ኦኩሙ ግድቡ የኢትዮጵያን እና የአፍሪካ ሀገራትን ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የሃይል አቅርቦቱ በቀጣናው ያለውን ኢንዱስትሪ ልማት እንደሚያፋጥንም ጠቁመዋል፡፡
የሕዳሴ ግድብ ባለፈዉ ሳምንት ጳጉሜን 4 ቀን 2017 በይፋ ሲመረቅ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የጂቡቲ ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌህ፣ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼኽ መሐመድ፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኬር፣ እና ሌሎች የአፍሪካ እና ካረቢያን ሀገራት መሪዎች መገኝታቸው ይታወቃል፡፡