በጋምቤላ ክልል ያለውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ የፀጥታ መዋቅሩ ይጠናከራል - ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል ያለውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ የፀጥታ መዋቅሩ ይጠናከራል - ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ

ጋምቤላ ፤መስከረም 2/2018 (ኢዜአ)፡-በጋምቤላ ክልል ያለውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ የፀጥታ መዋቅሩን የማጠናከሩ ተግባር እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለፁ።
በክልሉ የቦንጋ ፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋም የሰለጠኑ የአድማ ብተና የፖሊስ አባላትን ዛሬ አስመርቋል።
ወይዘሮ ዓለሚቱ በምረቃው ስነ-ስርዓቱ ላይ እንዳሉት በክልሉ ያለውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ የፀጥታ መዋቅሩን የማጠናከሩ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል።
የክልሉን ሰላም አስተማማኝ በማድረግ የተጀመረውን የልማትና የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ መንግስት በሁሉም መስኮች ያልተቆጠበ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
በተለይም የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ ባለፈ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩ በማድረግ ረገድ ስኬታማ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል ።
ክልሉ አሁን ላይ ያለውን ሰላም ለማፅናትና አስተማማኝ ለማድረግ ተጨማሪ የአድማ ብተና የፖሊስ አባላትን በማሰልጠን ለማስመረቅ መብቃቱን ተናግረዋል።
የዕለቱ ተመራቂ የአድማ ብተና የፖሊስ አባላትም በስልጠናው ያገኙትን ክህሎት ወደ ተግባር በመለወጥ የክልሉን ህዝብ ሰላምና ደህንነት በመጠበቅ ረገድ የተጣለባቸውን ኃላፊት በአግባቡ እንዲወጡ ርዕሰ መስተዳድሯ አስገንዝበዋል።
የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ማህበር ኮር በበኩላቸው በክልሉ ያለውን አስተማማኝ ሰላም ለማጽናት የፀጥታ መዋቅሩን የማጠናከርና ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት የመስራት ተግባር በመከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ዛሬ የተመረቁት የአድማ ብተና የፖሊስ አባላትም የዚሁ ጥረት አንዱ አካል መሆናቸውን ጠቁመው ይህም የፖሊስ ሰራዊቱን የማብቃት ተግባር ወደ ላቀ ደረጃ ያሳድገዋል ብለዋል።
በቦንጋ የፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋም ለሶስት ወራት ስልጠናቸውን የተከታተሉት የአድማ ብተና የፖሊስ አባላቱ በቆይታቸው የህግ፣ የሰብዓዊ መብትና መሠረታዊ የፖሊስ ሳይንስ ትምህርት የወሰዱ መሆናቸውም ተመላክቷል።