ዕድሜው ለትምህርት የደረሰ ልጅን ወደ ትምህርት ቤት አለመላክ ያስጠይቃል - ትምህርት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ዕድሜው ለትምህርት የደረሰ ልጅን ወደ ትምህርት ቤት አለመላክ ያስጠይቃል - ትምህርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ መስከረም 2/2018 (ኢዜአ)፦ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ነጻና ግዴታ መሆኑን በመገንዘብ ወላጅ ወይም አሳዳጊ ዕድሜው ለትምህርት የደረሰ ልጅን ወደ ትምህርት ቤት መላክ እንዳለበት ትምህርት ሚኒስቴር አሳሰበ።
በኢትዮጵያ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ከ7 ሚሊዮን በላይ ህጻናት በተለያዩ ምክንያቶች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን ሚኒስቴሩ መግለጹ ይታወቃል።
እነዚህን ልጆች ወደ ትምህርት ቤት የማስገባት ሀገራዊ ንቅናቄን በመቀላቀል የዜግነት ግዴታን በመወጣት ሁሉንም ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም አመላክቷል።
በሚኒስቴሩ የትምህርት ፕሮግራሞችና ሥርዓት ማሻሻል ዴስክ ኃላፊ ዳዊት አዘነ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ከቅድመ መደበኛ እስከ 8ኛ ክፍል ከተመዘገቡት ውስጥ ለ60 በመቶው የትምህርት ቤት ምገባ ተደራሽ ይደረጋል።
የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ነጻ እና ግዴታ መሆን በትምህርት ሕጉ መደንገጉን አስታውቀው፤ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት አለመላክ በሕግ እንደሚያስጠይቅም አሳስበዋል።
ወላጆች፣ አሳዳጊዎች፣ ሕብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆች ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይሆኑ ሊረባረቡ ይገባል ነው ያሉት።
በ2018 ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል 31 ነጥብ 9 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለማስተማር መታቀዱን እና ከእነዚህ መካከል 15 ሚሊዮኑ ሴቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ሰላም ባልተረጋገጠባቸው አካባቢዎች፣ በኢኮኖሚ እጥረት እና የልጆችን ጉልበት በመፈለግ ምክንያት በ2017 የትምህርት ዘመን ከ7 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ እንደነበሩም አውስተዋል።
በ2018 የትምህርት ዘመን በትምህርት ገበታ ላይ እንዲገኙ የታቀደው 31 ነጥብ 9 ሚሊዮንም ባለፈው ዓመት ከትምህርት ገበታ ውጭ የነበሩትን እንደሚያጠቃልል አስታውቀዋል።
ዕቅዱን ለማሳካትም ሚኒስቴሩ በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የተማሪዎች ተሳትፎ የንቅናቄ ሠነድ አዘጋጅቶ ከክልሎች እና ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ በማድረግ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ ለማስቻል ለማኅበረሰቡና ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ መፍጠር አንዱ የሠነዱ ትኩረት መሆኑን ጠቅሰዋል።
የተማሪ ተሳትፎ ዕቅድን ለማካካስ የሚያስችሉ ሁነቶችን ማዘጋጀት ሁለተኛው የሠነዱ ትኩረት መሆኑን ጠቁመው፤ የምዝገባ ሳምንት፣ የግቢ ጽዳት ሳምንት፣ የቤት ለቤት ቅስቀሳ እንዲሁም የትምህርት ቁሳቁስ የማሰባሰቢያ ሳምንት እንዲዘጋጁ ማድረግ መሆኑን አብራርተዋል።
ሦስተኛው ሰላምን የማጽናት ስራ እየተከናወነባቸው ባሉ አካባቢዎች ተማሪዎች በሚፈለገው ልክ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ በዋናነት የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ምቹ እንዲሆኑ እንዲሠሩ ማድረግ ነው ብለዋል።
ከነሐሴ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በመላው ሀገሪቱ የትምህርት ምዝገባ እና ተጓዳኝ ተግባራት በጥሩ ሁኔታ እየተከናወኑ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ሁሉም ትምህርት ቤቶች ከመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለትምህርት ክፍት ሆነው ማስተማር እንደሚጀምሩም አስታውቀዋል።