ቀጥታ፡

ደም በመለገስ የሰው ሕይወትን መታደግ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በኢሉባቦር ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ

መቱ፤ መስከረም 2/2018 (ኢዜአ)፡- በኢሉባቦር ዞን ደም በመለገስ የሰው ሕይወትን መታደግ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።

ከለጋሾቹ መካከል የሀሉ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ስንታየሁ ግርማ በደም እጥረት ለሚቸገሩ ወገኖች ደሙን በመለገሱ ደስተኛ መሆኑን አንስቶ ይህ መልካም ስራ ለአዕምሮ ዕረፍት ነው ብሏል።

"ልገሳውን እቀጥላለሁ" ያለው ወጣቱ ወጣቶችም ሆኑ ሌላው የሕብረተሰብ ክፍል በተግባሩ እንዲሳተፉ መልክት አስተላልፏል።

በተለይም በወሊድ ምክንያት የሚጎዱ እናቶችን ሕይወት ለመታደግ  በልገሳም ሆነ በማስተባበር የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ የገለጸው ደግሞ በመቱ ከተማ የወጣቶች አደረጃጀት ዘርፍ ተጠሪ ወጣት አቤኔዘር ተመስገን ነው።


 

የመቱ ደም ባንክ ስራ አስኪያጅ አቶ አማረ ደስታ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ በደም እጥረት ምክንያት ሊደርስ የሚችለውን ችግር ለመከላከል ሰባት ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በሚሰበሰበው ደም መቱ ከተማን ጨምሮ ኢሉባቦር፣ ቡኖ በደሌ እና ሸካ ዞኖችን ተደራሽ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ  የደም ለጋሾችን ለማብዛት የግንዛቤ ስራን ጨምሮ ሌሎች ስራዎችን በትኩረት እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

በአከባቢዎቹ በመደበኛነት ደም በመለገስ ከሚታወቁት ዜጎች ባሻገር በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ ወጣቶችና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ትልቅ እገዛ እያደረጉ እንደሚገኙም አክለዋል።

በ2017 በጀት ዓመት ከ5 ሺህ 900 በላይ ዩኒት ደም መሰብሰብ መቻሉን ገልጸው፤ በ2018 በጀት ዓመት ሰባት ሺህ  ዩኒት ደም ለመሰብሰብ አቅደው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም