ቀጥታ፡

በባሌ ዞን በሰው ሰራሽ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ዘዴ ውጤት እያገኙ መሆናቸውን አርሶ አደሮች ገለጹ

ሮቤ፤ መስከረም 2/2018(ኢዜአ) :-በሰው ሰራሽ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ዘዴ ጥሩ ውጤት እያገኙ መሆናቸውን በባሌ ዞን የዲንሾ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ። 

በዞኑ በተያዘው በጀት ዓመት ከ97 ሺህ የሚበልጡ የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል የወተትና ስጋ ተዋጽኦ ጥራትና መጠን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የገለጸው ደግሞ የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ነው። 

አስተያየታቸውን ከሰጡ የዲንሾ ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ሁሴን አብዱረህማን እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም ካላቸው ላሞች የሚያገኙት የወተት ምርት ከድካማቸው ጋር ሲነፃፀር እምብዛም አይደለም። 

ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ በሰው ሰራሽ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ዘዴ ከተዳቀሉ ከብቶቻቸው እያገኙ ያሉት የወተት ምርት በቀን በአማካይ ከሶስት ሊትር ወደ 15 ሊትር መጨመሩንና ተጠቃሚነታቸው ማደጉን ተናግረዋል። 

ከሶስት አመታት በፊት በዚህ ዘዴ ካዳቀሏት ላም የተገኘው ወይፈን ለእርሻ መድረሱን የጠቆሙት አርሶ አደሩ፤ በዘርፉ የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን ሌሎች ለሞቻቸውን እያዳቀሉ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

ወይዘሮ አሽረቃ ሱሌይማን  በበኩላቸው በሰው ሰራሽ ዘዴ ከተዳቀሉ ላሞቻቸው እያገኙ ያሉት የወተት ምርት መጠን በቀን በአማካይ ከሶስት ወደ 10 ሊትር የጨመረ መሆኑን አንስተው፤ በዚህም የተሻለ ጥቅም  ማግኘታቸውን ተናግረዋል። 

ከላሞቻቸው የሚያገኙትን ወተት በማኮናተር በሚያገኙት ገቢ በዲንሾ ከተማ የተሻላ መኖሪያ ቤት ከመሥራት ባለፈ ልጆቻቸውን በተሻለ ትምህርት ቤት እያስተማሩ መሆኑን አክለዋል። 

ከዚህ በፊት የነበራቸው የአካባቢው ዝርያ ላሞች የሚወልዷቸው ጥጆች አድገው በገበያ ጥሩ ገንዘብ ለማስገኘትም ሆነ የወተት ምርት የሚሰጡበት ጊዜ ከተዳቀሉት ጋር ሲነፃፀር ረዥም ጊዜ የሚያስጠብቅ መሆኑን ያነሱት ደግሞ ሌላው የወረዳው አርሶ አደር አቶ ተማም ጀማል ናቸው።  

በሰው ሰራሽ ዘዴ ተዳቅለው የሚወለዱ ጊደሮች ከሶስት ዓመት በታች በሆነ ጊዜ የሚወልዱ መሆናቸውን በማሳያነት አንስተዋል። 

የዲንሾ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርናና መሬት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዙቤር አብዱለጥፍ በበኩላቸው፣ በሰው ሰራሽ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ዘዴ የሚዳቀሉ ከብቶች ውጤታማነት ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።

በባህላዊ ዘዴ ከሚደረገው የእንስሳት ልማት የተሻለ የወተትና የስጋ ምርት እንደሚያስገኝ በመረጋገጡም የተጠቃሚ አርሶ አደሩ ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል። 

በተያዘው በጀት ዓመትም በወረዳው ከ12ሺህ የሚበልጡ ላሞች በሰው ሰራሽ ዘዴ በማዳቀል የተሻለ የወተትና የስጋ ምርት ለማግኘት ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል። 

በዞኑ በተያዘው ዓመት ከ97 ሺህ በላይ የሚሆኑ ላሞችን በሰው ሰራሽ ዘዴ ለማዳቀል ታቅዶ ወደ ስራ የተገባ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የባሌ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሙአዊያ ፉኣድ ናቸው። 

የእንስሳትና እንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን መጠንና ጥራት በመጨመር የአርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የእንስሳት ዝርያን በሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የማሻሻል ስራ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

በዞኑ ከአካባቢው ላሞች በቀን የሚገኘው የወተት ምርት ከሶስት ሊትር እንደማይበልጥ የገለጹት ምክትል ሀላፊው በሰው ሰራሽ ስነ-ዘዴ ከተዳቀሉ ላሞች የሚገኘው የወተት ምርት በቀን በአማካይ ከ12 እስከ 15 ሊትር መሆኑን በማሳያነት አንስቷል።

አቶ ሙአዊያ እንዳሉት በዞኑ በሰው ሰራሽ ዘዴ ከሚዳቀሉ ላሞች የሚገኘውን የወተት ምርት ከማሳደግ በተጓዳኝ በበጀት ዓመቱ ከ45 ሺህ 600 የሚበልጡ ጥጆችን ለማግኘት መታቀዱንም አክለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም