የሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያውያን አልፎ ቀጣናዊ ትስስርን ያጠናክራል - በኢትዮጵያ የጀርመን ምክትል አምባሳደር ፈርዲናንድ ፎን ቫሄ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያውያን አልፎ ቀጣናዊ ትስስርን ያጠናክራል - በኢትዮጵያ የጀርመን ምክትል አምባሳደር ፈርዲናንድ ፎን ቫሄ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መስከረም 2/2018 (ኢዜአ)፦ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት ባለፈ የቀጣናው ሀገራትን ለማስተሳሰር ትልቅ አቅም ያለው መሆኑን በኢትዮጵያ የጀርመን ምክትል አምባሳደር ፈርዲናንድ ፎን ቫሄ (ዶ/ር) ገለጹ።
ኢትዮጵያ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የተመቸች ሀገር መሆኗንም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ መመረቃቸው ይታወቃል።
የሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ መመረቅን አስመልክቶ ኢዜአ በኢትዮጵያ የጀርመን ምክትል አምባሳደር ፈርዲናንድ ፎን ቫሄ (ዶ/ር)ን አነጋገሯል።
ምክትል አምባሳደሩ እንደገለጹት፤ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ቀጣናውንና ሌሎች አገራትን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ትስስርንም የሚያጠናክር ነው።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ከፍተኛ የአሌትሪክ ሀይል የማመንጨት አቅም ያለው መሆኑን ገልጸው፤ ጎረቤት አገራትም ሆኑ ከዚያም ባለፈ መልኩ በትብብር ከሰሩ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ ይችላሉ ብለዋል።
ግድቡ በኢትዮጵያውያን ትብብር እውን መሆኑን አውቃለሁ ያሉት አምባሳደሩ፤ በአሁኑ ወቅትም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ለምረቃ መብቃቱ የሚያኮራና የሚያስደስት ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የካርበን ልቀትን ለመቀነስ፣ የታዳሽ ሀይል አጠቃቀምን ለማስፋፋት የሚከናወኑ ስራዎችን መመልከታቸው ገልጸው፤ ይህም የሚበረታታ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያና ጀርመን በፀሐይና በሌሎች ታዳሽ የሀይል አማራጮች ላይ ጥናትና ምርምር እየሰሩ እንደሚገኙ አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የተከናወኑ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ተስፋ የሚሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።
የህግ ማዕቀፍ መሻሻል፣ በርካታ የሰው ሀይል መኖሩና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸው ለባለሀብቶች ኢንቨስት ለማድረግ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ናቸው ብለዋል።