በመዲናዋ የ2018 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል የእሳት አደጋ አልደረሰም - የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ የ2018 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል የእሳት አደጋ አልደረሰም - የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን

አዲስ አበባ፤ መስከረም 2/2018 (ኢዜአ)፦ በመዲናዋ የ2018 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል የጎላ የእሳት አደጋ ክስተት ሳይደርስ በሰላም መከበሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሞያ ንጋቱ ማሞ እንደገለጹት፤ የ2018 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል ሊኖር ከሚችል የአደጋ ተጋለጭነት አንጻር በዓሉ በሰላም ተከብሮ አልፏል ብለዋል።
የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በዓሉ ያለ አደጋ ክስተት ተከብሮ እንዲያልፍ በተለያዩ አማራጮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ሲሰጥ መቆየቱን ጠቀሰው፤ ህብረተሰቡ ከኮሚሽኑ ሲተላለፉ የነበሩ የጥንቃቄ መልዕክቶችን በመተግበሩ በዓሉ በሰላም መከበሩን ገልጸዋል።
በዋዜማው ሌሊት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ብሄረ ጽጌ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የእሳት አደጋ ተከስቶ የነበረ ቢሆንም የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች አደጋው ቦታ ፈጥነው በመድረስ እሳቱ ሳይስፋፋ መቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል።
በአደጋው በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ጠቅሰው፤ በንብረት ላይ አነስተኛ ጉዳት ማስከተሉን ተናግረዋል።
ህብረተሰብ በዓሉ ከአደጋ ተጠብቆ እንዲያልፍ ላደረገው አስተዋጾ አመስግነው በቀጣይ በዓላት እና በመደበኛ እንቅስቃሴዎችም ጥንቃቄዎች ባህል ሆነው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በመጪው የመስቀልና የኢሬቻ በዓልም አደጋ ሳይከሰት በሰላም እንዲያልፍ ከወዲሁ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።
አደጋን ቀድሞ ለመከላከል ህብረተሰቡን የማስገንዘብ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ ህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ መገልገያዎችንና ከሰል ሲጠቀም ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ መክረዋል።