ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለቀጣናው ጥብቅ ትስስር ከፍተኛ ሚና አለው- ላውረንስ ፍሪማን - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለቀጣናው ጥብቅ ትስስር ከፍተኛ ሚና አለው- ላውረንስ ፍሪማን

አዲስ አበባ፤ መስከረም 2/2018(ኢዜአ)፡- የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ትሩፋት ለጎረቤት ሀገራት ጭምር በመሆኑ ትስስሩን በማጠናከር ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን አሜሪካዊው የፖለቲካል ኢኮኖሚክ ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን ገለጹ።
ላውረንስ ፍሪማን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በአፍሪካ ትልቁን የኃይል ማመንጫ ግድብ በስኬት ማጠናቀቅ ልዩ ብርታት እንደሚሻ አንስተዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መመረቁ ይታወቃል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቅቆ መመረቅ አፍሪካ እንደምትችል ምስክር ሆኖ የሚነሳ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ግድቡ 5 ሺህ 150 ሜጋዋት የማመንጨት አቅም እንዳለው ጠቅሰው፤ ይህም ለቀጣናው ሀገራት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኙበት ተጨማሪ በጎ ዕድል ስለመሆኑም አስገንዝበዋል።
በሌላ በኩል እንደ ሀገር ተጨማሪ ኃይል አግኝቶ ከመጠቀም ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት በመሸጥ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በማሳደግ ረገድ የራሱን ሚና እንደሚያበረክትም ተናግረዋል።
የኃይል ተደራሽነትን ጨምሮ ፍላጎቶችን በራስ አቅም ለመሸፈን በሚደረጉ ጥረቶች ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አህጉር በአርዓያነት የሚጠቀሱ ተግባራት እያከናወነች እንደምትገኝም አመላክተዋል።
አንድ መታወቅ ያለበት ሐቅ አለ ያሉት ላውረንስ ፍሪማን፤ ግድቡ በተፋሰሱ ሀገራት ግብጽና ሱዳን ምንም ዓይነት ጉዳት አለማድረሱ ነው ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል።
ለዚህ ደግሞ ውኃው ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያ ውስጥ አለመቅረቱን ዐይቻለሁ በማለት የግድቡ ዓላማም ውኃውን ማስቀረት እንዳልሆነ አስረድተዋል።
በመሆኑም ውኃው በተፈጥሯዊ ፍሰቱ ወደ ተፋሰሱ ሀገራት ግብጽና ሱዳን ጉዞውን ያለማቋረጥ መቀጠሉን ነው የተናገሩት።
ሰዎች ተፈጥሮን ለተሻለ ነገር ማዋል እንደሚችሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፤ እርሳቸው ሁለት ጊዜ እንደጎበኙት እና አፍሪካውያን ብሎም አውሮፓውያን ይህን ድንቅ ግድብ ሊጎበኙት እንደሚገባ መክረዋል።