ቀጥታ፡

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የተመዘገበው ድል ለሌሎች ስኬቶች መነሳሳትን የፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 2/2018 (ኢዜአ)፦ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተመዘገበው ድል መነሳሳትን የፈጠረና ለሌሎች ፕሮጀክቶች ከፍ ያለ እሳቤን ያጎናጸፈ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት መጠናቀቅን ምክንያት በማድረግ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት የማስ ስፖርት ተካሂዷል።

በመርሃግብሩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ወጣቶች የስፖርት ቤተሰቦች እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ህልማቸውን በጋራ ያሳኩበት ፕሮጀክት ነው።

የከተማዋ ነዋሪም ለስኬቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ በመንቀሳቀስ ግድቡ እውን እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

በሕዳሴ ግድብ የተመዘገበው ድልም ለሌሎች ስኬቶች መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑን አመልክተው፤ በቀጣይ ለሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ከፍ ያለ እሳቤን የፈጠረ ነው ብለዋል።

ግድቡ ኢትዮጵያውያን እንደሚችሉ ለዓለም ያሳዩበትና ህልማቸውን በጋራ ያሳኩበት ፕሮጀክት መሆኑንም ጠቅሰው፤ ከትንሽ እስከ ትልቅ ከሀብታም እስከ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ኢትዮጵያውያን በመረባረብ በጋራ ያሳኩት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አሁንም በሌሎች የልማት ስራዎች ላይ በህብረት ይበልጥ መረባረብ አለብን ብለዋል።


 

በመርሀግብሩ ላይ ያገኘናቸው ሳሙኤል በቀለ እና እጸገነት ወልዴ በሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የአንድነት ምልክት መሆኑንም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም