ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የጀመረቻቸውን ኢንሼቲቮች በደቡብ ደቡብ ትብብር ማጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የጀመረቻቸውን ኢንሼቲቮች በደቡብ ደቡብ ትብብር ማጠናከር ይገባል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 2/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የጀመረቻቸውን ኢንሼቲቮች በደቡብ ደቡብ ትብብር ማጠናከር እንደሚገባ የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ገለጹ፡፡
የአፍሪካ የበካይ ጋዝ ልቀት መጠን ከአራት በመቶ ባይበልጥም በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ከፍተኛ ተጎጂ መሆኗ አልቀረም፡፡
በተለይም አፍሪካን ጨምሮ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የሚደርስባቸውን ችግር የህልውና ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ሆኗል፡፡
አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የጎላ በካይ ጋዝ ከሚለቁ ሀገራት ከመጠበቅ የራሷን መፍትሔ መፈለግ አለባት የሚለው የብዙ ዓለም አቀፍ ተቋማት ምክረ ሀሳብ ነው፡፡
ከዚህ ባሻገር እንደ ቻይና እና ጃፓን በቴክኖሎጂ ከበለጸጉ ሀገራት ጋር በደቡብ ደቡብ ትብብር የቴክኖሎጂ አቅምን ማሳደግ እንደሚገባም ይገልፃሉ፡፡
የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ረዳት ዋና ጸሀፊ ቶማስ አሳሬ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአየር ንብረት ፋይናንስ በማመንጨት እና ጎረቤት ሀገራት በታዳሽ ኃይል በማስተሳሰር የጎላ አበርክቶ አለው፡፡
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በቢሊዬን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ እየገነባች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአመራር ቁርጠኝነት እና የኢትዮጵያ ህዝብ ተሳትፎ የላቀ አበርክቶ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም የምታደርገውን ጥረት በደቡብ ደቡብ ትብብር ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡
የዓለም የእርሻና ምግብ ድርጅት ረዳት ዳይሬክተር ጀነራል እና የአፍሪካ ተጠሪ አበበ ኃይለገብርኤል (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስን ከፍተኛ በካይ ጋዝ የሚለቁት ያደጉ ሀገራት እንዲሸፍኑ የወጡ የፓሪስ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በአግባቡ ገቢራዊ አልተደረጉም ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የደቡብ ደቡብ ትብብርን በማጠናከር የቴክኖሎጂ አቅማቸውን ማሳደግ እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡
አፍሪካ የታዳሽ ሀይል፣ እምቅ የማዕድንና ሌሎች የተፈጥሮ ጸጋዎች ያሏት አህጉር መሆኗን በመጥቀስ፤ በደቡብ ደቡብ ትብብር ጸጋዋን የምትጠቀምበት ቴክኖሎጂ ማላመድ አለባት ብለዋል፡፡
በደቡብ ደቡብ ትብብር ማዕቀፍ እንደ ቻይና ያሉ ሀገራት በብዙ ተፈትነው መሰረት የያዘ የቴክኖሎጂ አቅም ገንብተዋል ያሉት ዶክተር አበበ ፤ አፍሪካ ዘግይታ መግባቷን /late comer advantage/ እንደ እድል መጠቀም እንዳለባት ገልጸዋል፡፡