ህብረተሰቡ የአካል ጉዳተኞችን መብትና ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ ሚናውን የበለጠ ማጠናከር አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ህብረተሰቡ የአካል ጉዳተኞችን መብትና ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ ሚናውን የበለጠ ማጠናከር አለበት
አዲስ አበባ፤ መስከረም 1/2018 (ኢዜአ)፦ ህብረተሰቡ የአካል ጉዳተኞችን መብትና ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ ሚናውን የበለጠ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ( ዶ/ር) ተናገሩ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራር አባላት ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ብሔራዊ ማህበር ጋር በመሆን የ2018 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓልን ከሴት አካል ጉዳተኞች ጋር አክብረዋል።
በመርኃ ግብሩ ላይ የማዕድ ማጋራት፣ በማህበሩ ስር ላሉ ሴት አካል ጉዳተኛ ህፃናት የተለያዩ የአካል ድጋፍ እና የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ እና በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ሴት አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ሽልማት ማበርከት ተካቷል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ( ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተመረቀበት ወቅት ላይ የዘመን መለወጫ በዓልን ማክበር ልዩ ስሜት ይፈጥራል።
ህብረተሰቡ የአካል ጉዳተኞችን መብትና ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ ሚናውን የበለጠ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ሚንስትሯ አስገንዝበዋል።
የ2018 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት በአንድነት በመስራት እንደ ሀገር የተቀመጡ የልማት ግቦችን የምናሳከበት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
መንግሥት የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን ከአካል ጉዳተኞች ማህበራት ጋር በመሆን አጠናክሮ መቀጠሉንም ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ብሔራዊ ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ድባቤ ባጫ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ በመመረቁ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ማህበሩ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ የሴት አካል ጉዳተኞች ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ እየሠራ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
ማህበሩ በየዓመቱ የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለአካል ጉዳተኞች የማዕድ ማጋራት መርሀ ግብር እንደሚያካሂድ ገልፀው፤ የዘንድሮ አዲስ ዓመት በዓልን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በማክበራቸው ደስታ እንደተሰማቸውም ተናግረዋል።
በመርሀ ግብሩ ላይ የተሳተፉት ወይዘሮ አባይነሽ አየለ፤ የ12 ዓመት ሴት ልጃቸው መራመድ ባለመቻሏ ማህበራዊ ህይወታቸውን ለመምራት አዳጋች ሆኖባቸው መቆየቱን ያስታውሳሉ።
የአዲስ ዓመት መለወጫ በዓልን በማስመልከት ለልጃቸው የዊልቸር ሽልማት በማግኘታቸው ሁለቱንም ከእንግልት እና ድካም እንደሚታደጋቸው ተናግረዋል።
ቆንጂት ጌታቸው በበኩሏ፤ ካለባት የአካል ጉዳት አኳያ የአካል ድጋፍ መሳሪያ ማግኘቷ የሰው እገዛ ሳትፈልግ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ አቅም እንደሚፈጥርላት ገልጻለች።
በተያያዘ ዜና በ22ኛው በተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል ገላን ጉራ ቅርንጫፍ የማዕድ ማጋራት ተካሂዷል።
በመርሀ ግብሩ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ጥራቱ በየነ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ይመር ከበደ ተገኝተዋል።
በመርሀ ግብሩ ላይ የተሳተፉት አቶ አበበ በቀለ ዝግጅቱ ደስታ እንደፈጠረላቸው ገልጸው፤ እንዲህ ዓይነት መተባበር እና መደጋገፍ ትልቅነት መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ ፋንታዬ ዳምጠው፤ በምገባ ማዕከሉ በየቀኑ አገልግሎት እንደሚያገኙ ገልጸው፤ ያለምንም እንከን እየተመገቡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
በዛሬው ዕለት የተደረገው የበዓል ምገባም ደስታን እንደፈጠረላቸው እና ይህንን ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
በዓሉን በደስታ እያሳለፉ መሆኑን የገለጹት ተስፋነሽ ታደሰ እና ደሊል ዑስማን ናቸው።