ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ ውድድር ተሰናበተ 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 1/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በምድብ ሁለት በካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ከብሩንዲው ቶፕ ገርልስ አካዳሚ ጋር ያደረገው ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ጨዋታው በካሳራኒ ስታዲየም ተከናውኗል። 

ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአንድ ነጥብ የመጨረሻውን ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ከውድድሩ ውጪ ሆኗል። ቡድኑ በማሸነፍ ምርጥ ሁለተኛ ሆኖ የማለፍ እድሉን አልተጠቀመበትም። 

ንግድ ባንክ በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታው በሩዋንዳው ራዮን ስፖርት 2 ለ 1 መሸነፉ የሚታወስ ነው።

በምድብ ሁለት ራዮን ስፖርት በአራት ነጥብ ለግማሽ ፍጻሜ አልፏል። 

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው የሴካፋ ዞን ማጣሪያ በማሸነፍ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ መሳተፉ የሚታወስ ነው።

የምድብ ጨዋታዎች ዛሬ ይጠናቀቃሉ። የግማሽ ፍጻሜ መርሃ ግብር መስከረም 4 ቀን 2018 ዓ.ም ይከናወናል።

በኬንያ እየተካሄደ የሚገኘው የሴካፋ ዞን ማጣሪያ እስከ መስከረም 6 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን ማጣሪያውን የሚያሸንፍ ክለብ ሴካፋን ወክሎ በካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ይሳተፋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም