ቀጥታ፡

መንግሥት የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሠራ ነው- ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 1/2018(ኢዜአ)፦መንግሥት የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና የልማት ተሳትፎ ለማጠናከር በትኩረት እየሠራ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ  ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ።

የሴቶችና ማህበራዊ  ጉዳይ ሚኒስቴር አመራሮች ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ብሔራዊ ማህበር ጋር በመሆን የ2018 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓልን በመዲናዋ ከሚገኙ ሴት አካል ጉዳተኞች ጋር አክብረዋል።

በመርኃ ግብሩ የማዕድ ማጋራት፣ በማህበሩ ስር ላሉ ሴት አካል ጉዳተኛ ህፃናት የተለያዩ የአካል ድጋፍ እና   የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍና በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ሴት አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ሽልማት ተበርክቷል።


 

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ( ዶ/ር) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተመረቀበት ወቅት ላይ የዘመን መለወጫ በዓልን ማክበር ልዩ ስሜት እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

አካል ጉዳተኞች በልማት ሥራ  ጉልህ ተሳተፎ እያደረጉ መሆኑን ገልጸው፥ መንግሥት ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጡ ተግባራትን ከአካል ጉዳተኞች ማህበራት ጋር በመሆን አጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ብሔራዊ ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ ድባቤ ባጫ፥ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በመጠናቀቁ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።


 

ማህበሩ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ የሴት አካል ጉዳተኞች ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ማህበሩ በየዓመቱ የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለአካል ጉዳተኞች የማዕድ ማጋራት መርሀ ግብር እንደሚያካሂድ ገልፀው የዘንድሮ አዲስ ዓመት በዓለን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በማክበራችን ደስ ብሎናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም