ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የዚህ ትውልድ ደማቅ የታሪክ አሻራ እና ቋሚ ቅርስ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የዚህ ትውልድ ደማቅ የታሪክ አሻራ እና ቋሚ ቅርስ ነው
ወልቂጤ፤ መስከረም 1/2018 (ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የዚህ ትውልድ ደማቅ የታሪክ አሻራ እና ቋሚ ቅርስ መሆኑ ተገለጸ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም የተለያዩ አገራት መሪዎች በተገኙበት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቋል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የግድቡ መጠናቀቅ ከኢኮኖሚ ጥቅም ባለፈ በቀጣናዊ የልማት ትስስርና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት አንፃር ወሳኝ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ፍቃዱ ማሞ፤ የህዳሴ ግድብ የዚህ ትውልድ ደማቅ የታሪክ አሻራና ቋሚ ቅርስ መሆኑን ገልጸዋል።
የግድቡ ግንባታ በሀገር ልጆች ጥሪት፣ እውቀትና ጉልበት ብዙ ፈተናዎችን በመጋፈጥ የተሰራ ግዙፍ ፕሮጀክት በመሆኑ ሁላችንንም አኩርቷል ብለዋል።
የህዳሴ ግድብ የብርሃን ምንጭ፣ የንጋት ባህር የዓሳ ሃብት፣ የቱሪዝም መስህብ ስፍራ በመሆን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ፕሮጀክት መሆኑንም አንስተዋል።
በመሆኑም የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ የኢትዮጵያ የእድገትና ለውጥ ምልክት መሆኑን ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው የህክምና ኮሌጅ መምህር የሆኑት በረከት ዘለቀ፤ በበኩላቸው የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የአንድነት ማሳያ እና የፅናት ምልክት መሆኑን ተናግረዋል።
የዚህ ግዙፍ ግድብ ግንባታ ስኬት ለሌሎች ግዙፍ የግንባታ ፕሮጀክቶች ልምድና እውቀት የተገኘበት የመቻል አቅም ማሳያ መሆኑንም አንስተዋል።
በመሆኑም የተገኙ ስኬቶችን በማስቀጠል ለሀገር ልማት፣ እድገትና ብልጽግና በጋራ ትጋታችንን አጠናክረን መቀጠል አለብን ብለዋል።
ሌላኛው የዩኒቨርሲቲው መምህር ዘሪሁን ሙሉጌታ፤ የግድቡ መጠናቀቅ በትክክልም የኢትዮጵያ የማንሰራራት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
ከኤሌክትሪክ ሃይል ምንጭነት በተጨማሪ የተፈጥሮ ምህዳርን የጠበቀ፣ በአካባቢው የአረንጓዴ ልማትና ልምላሜን የሚያስጠብቅ እምቅ ሃብት መሆኑንም አንስተዋል።
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዮሃንስ ገብሩ (ዶ/ር) አባይን ለመጠቀም ለዘመናት የተደረጉ ጥረቶች ሳይሳኩ ቀርተው በዚህ ትውልድ እውን መሆኑ በራሱ አዲስ ታሪክ መሰራቱን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
በዚህ ሂደት የመንግስት ቁርጠኝነት፣ የህዝቡ ትጋት፣ ጥረትና ትብብር አስደናቂ መሆኑን አንስተው በጋራ መቆም ከተቻለ የማናሳካው ልማት እንደሌለ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።