የ2018 አዲስ ዓመት የሀገራችንን ከፍታ ይበልጥ የምናጎላበት ይሆናል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የ2018 አዲስ ዓመት የሀገራችንን ከፍታ ይበልጥ የምናጎላበት ይሆናል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 1/2018(ኢዜአ)፦ የ2018 አዲስ ዓመት የኢትዮጵያ ማንሠራራት በጠንካራ መሠረት የሚገነባበት፣ የሀገራችን ከፍታ የሚጎላበትና የዜጎች ተጠቃሚነት ይበልጥ የሚረጋገጥበት ዓመት ይሆናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለመላው ኢትዮጵያውያንና ለመዲናዋ ነዋሪዎች ለ2018 ዓ.ም አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም የ2018 አዲስ ዓመትን የተቀበልነው የሁላችንም አሻራ ያረፈበት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በድል አድራጊነት በማጠናቀቅ በመሆኑ እንኳን ደስ አላችሁ፣ እንኳን ደስ አለን ብለዋል።
በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በስንዴ፣ በከተማ ልማት በተለይም አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ ያደረጉ ትልልቅ ስኬቶች መመዝገባቸው የበለጠ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንድንሠራ ትጥቅና መሰረት መሆናቸውን ገልጸዋል።
የ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ማንሠራራት መሰረት እጅግ ከፍ ብሎ የሚገነባበት፣ ሁለንተናዊ ብልፅግናን የማፋጠን ጉዞ በስኬት የምናስቀጥልበት ነው ብለዋል።
የሀገራችንን ከፍታና የዜጎችን ተጠቃሚነት ከዚህ በላይ በማጉላት ኢትዮጵያን ከድህነትና ከጉስቁልና ለማውጣት ተባብረን መስራት አለብን ነው ያሉት።
በርካታ የታሪክ እጥፋቶችን ደግመን ደጋግመን በድል አድራጊነት እንድናስመዘግብ አደራ እላለሁ ብለዋል።
አዲሱ ዓመት ሠርተን ውጤታማ የምንሆንበት፣ ሰላማችንን ዘላቂና አስተማማኝ የምናደርግበት፣ ለሁላችንም የሚመችና ስኬቶቻችን ጎልተው የሚወጡበት ዓመት እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።