የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ ከቶፕ ጋርልስ አካዳሚ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ይጠበቃል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ ከቶፕ ጋርልስ አካዳሚ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ይጠበቃል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 1/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታውን ዛሬ ከብሩንዲው ቶፕ ገርልስ አካዳሚ ጋር ይጫወታል።
ጨዋታው ከቀኑ 7 ሰዓት በካሳራኒ ስታዲየም ይካሄዳል።
የሴካፋ ዞን ማጣሪያ በኬንያ እየተካሄደ ይገኛል።
ኢትዮጵያን በሴካፋ ዞን ወክሎ በማጣሪያ ውድድሩ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በምድብ ሁለት ሁለተኛ እና የመጨረሻ ጨዋታውን ከብሩንዲው ቶፕ ገርልስ አካዳሚ ጋር ያከናውናል።
በብርሃኑ ግዛው የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመጀመሪያ ጨዋታው በሩዋንዳው ራዮን ስፖርት 2 ለ 1 መሸነፉ ይታወቃል።
ተጋጣሚው ቶፕ ገርልስ አካዳሚ በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታው ከራዮን ስፖርት ጋር ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይቷል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከምድቡ ምርጥ ሁለተኛ ሆኖ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ለማለፍ የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅበታል።
ንግድ ባንክ በ2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው የሴካፋ ዞን ማጣሪያ በማሸነፍ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ መሳተፉ የሚታወስ ነው።
የሩዋንዳው ራዮን ስፖርት ምድቡን በአራት ነጥብ እየመራ ይገኛል።
በምድብ አንድ የሚገኘው የኬንያው ኬንያ ቡሌትስ በስድስት ነጥብ ወደ ግማሽ ፍጻሜው የገባ የመጀመሪያ ቡድን ሆኗል።
በውድድሩ ላይ ዘጠኝ ሀገራት በሶስት ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን እያካሄዱ ይገኛል።
የሴካፋ ዞን ማጣሪያ እስከ መስከረም 6 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል። ማጣሪያውን የሚያሸንፍ ክለብ ሴካፋን ወክሎ በ2025/26 የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ ይሳተፋል።