ቀጥታ፡

የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች እና አምባሳደሮች ለ2018 አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 1/2018(ኢዜአ)፦ ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች እና አምባሳደሮች ለ2018 አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያውያን የደስታ እና የብልጽግና እንዲሆን ተመኝቷል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ አዲስ ዓመት ተስፋችንን ዳግም የምናድስበት እና ትስስራችንን የበለጠ የምጠናክርበት እንደሚሆን አምናለሁ ብለዋል።  

አዲሱ ዓመት ሰላም እና ብሩህ መጻኢ ጊዜ በጋራ የምንገነባበት ይሁንልን ሲሉም አምባሳደሩ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል። 

ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ለ2018 ዓ.ም አዲስ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ ያለው ደግሞ በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ ነው።
አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የእድገት እና የብልጽግና እንዲሆንም ተመኝቷል። 

ኤምባሲው በመልካም ምኞት መግለጫው እስራኤል በአዲሱ ዓመት ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ጥብቅ ግንኙነትና ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለችም ነው ያለው። 

በኢትዮጵያ የአርሜኒያ አምባሳደር ሳሃክ ሳርጌሲያን ለኢትዮጵያውያን እህቶች እና ወንድሞቼ መልካም አዲስ ዓመት ይሁንላችሁ ሲሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የ13 ወር ጸጋ ያላት ልዩ ሀገር ናት ያሉት አምባሳደሩ ኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመትን ባህላዊ ልብሶች እና ምግቦችን ጨምሮ በተለያዩ የእሴት መገለጫዎችን በጋራ በመሆን የሚያከብሩበት መንገድ የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እና አርሜኒያ ዘመናትን የተሻገረ ታሪካዊ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ጠቅሰው አዲሱ ዓመት ለሁለቱም ሀገራት ህዝቦች የሰላምና የስኬት እንዲሆን ተመኝተዋል።

አዲስ ዓመት ለኢትዮጵያውያን የሰላም እና የጤና እንዲሆን እመኛለሁ ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
17ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የብዝሃ ህይወት ጉባኤ(ኮፕ 17) ፕሬዝዳንት የሆነችው አርሜኒያ ዋና ተደራዳሪ

አምባሳደር መኸር ማርጋሪያን በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን ይበልጥ ከተፈጥሮ ሀብታቸው ጋር ተወዳጅተው የሚኖሩበት ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል።

በተለይም ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም እና በመንከባከብ እንዲሁም በአይበገሬነት ስሜትና በበለጠ ደስታ እንዲያከብሩት ጽኑ ምኞቴ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የዩናይትድ ኪንግደም ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ ሉክ ቡሎክ በመልካም ምኞት መልዕክታቸው

ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ኪንግደም የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ያከናወኗቸው ስራዎች ፍሬያማ ነበሩ ብለዋል።

ዩናይትድ ኪንግደም ከኢትዮጵያ ጋር በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል፣ ንግድ እና ስደተኞች ጉዳይን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ያላትን ትብብር ለማጎልበት እንደምትሻ አመለክተዋል።

ምክትል ሚሲዮን መሪው አዲሱ ዓመት የሰላም እና የጤና እንዲሆንም ተመኝተዋል። 
በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ ኤምባሲ አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያውያን የሰላም፣ የደስታ እና የብልጽግና እንዲሆን መልካም ምኞቱን ገልጿል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ አዲሱ ዓመት የደስታ እና የሰላም እንዲሆን መልካም ምኞቱን ገልጿል። 

የአውሮፓ ህብረት ለ2018 ዓ.ም አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል። 
የህብረቱ የኢትዮጵያ ልዑክ ባስተላለፈው የመልካም ምኞት መልዕክት አዲሱ ዓመት ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የሰላም እና የደስታ እንዲሆን ተመኝቷል። 

በኢትዮጵያ የስዊድን፣ ኔዘርላንድስ፣ ስዊዘርላንድ እና ካናዳ  ኤምባሲዎችም የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መግለጫቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም