ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አዲሱን ዓመት በድል ያበሰረና በኅብረት የሀገራችንን የከፍታ ጉዞ እንደምናሳካ ያሳየ ነው - የመዲናዋ አመራሮች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 1/2018(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አዲሱን ዓመት በድል ያበሰረና በኅብረት የሀገራችንን የከፍታ ጉዞ እንደምናሳካ ያሳየ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች ገለፁ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ መመረቃቸው ይታወቃል።


 

በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ስራ አስኪያጅ ተፈራ ሞላ ለኢዜአ እንዳሉት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ አንድምታው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ግድቡ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ፕሮጀክትን ጀምራ እንደምትጨርስ እንዲሁም የራሷን ኢኮኖሚ ራሷ መገንባት እንደምትችል ያሳየ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን ስንተባበር አሸናፊ እንደምንሆን ያሳየና ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን በመጠቆም ግድቡ ለከፍታችን መሰረት በዲፕሎማሲ መስክም ውጤታማ የሆንበት ነው ብለዋል።

በመንግሥትና በሕዝብ የተባበረ አቅም ሀገራዊ ግቦችን ማሳካት እንደሚቻል ያሳየ መሆኑንም ነው አቶ ተፈራ ሞላ ጨምረው የተናገሩት።


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና ድንገተኛ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽነር ኮማንደር አህመድ መሐመድ በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመሆን ይቻላልን ያሳዩበት ነው ብለዋል።

በጋራ ከሰሩ ማሸነፍ እንደሚቻል ያስመሰከረና ሌሎች ፕሮጀክቶችን በስኬት ማጠናቀቅ የሚያስችል ትምህርት የተገኘበት መሆኑንም ገልፀዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአንድነታችን የስኬትና ውጤት ትዕምርት ነው ሲሉም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ትውልዱ ሀብትና እውቀቱን በአግባቡ በመጠቀም ኢትዮጵያን ካደጉ ሀገራት ተርታ ማሰለፍ እንደሚችል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማሳያ መሆኑንም አመራሮቹ ገልጸዋል።

ግድቡ አዲሱን ዓመት በድል ያበሰረ ነው ያሉት አመራሮቹ፥ ዛሬ በጀመርነው 2018 አዲስ ዓመት ሁላችንም በአንድነት ለሀገር ልማትና የከፍታ ጉዞ መሳካት በጊዜ የለንም መንፈስ መትጋት አለብን ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም