ሰዎች ወደ አዲሱ ዓመት ምን ያሻግሩ? - ኢዜአ አማርኛ
ሰዎች ወደ አዲሱ ዓመት ምን ያሻግሩ?
አዲስ ዓመትን በአዲስ ሥነ-ልቦናዊ ዝግጅት መቀበል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን እንደሚያስገኝ የሥነ-ልቦና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
በሀገራችን የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ አዲስ ዓመትን በአዳዲስ አልባሳት ተውቦ ለመቀበል ቀደም ብሎ መዘጋጀት የተለመደ ነው።
ከዚህ ጎን ለጎን ዘመኑን ያልዋጀ እሳቤን ከጊዜው ጋር በሚጣጣምና ለብዙኃን በሚተርፍ መልካም ዕሳቤ መቀየር እንደሚገባ በኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል የተሃድሶ ሕክምና አስተባባሪ፣ ክሊኒካል ሳይኮሎጂስት እና የሳይኮሎጂካል ትራውማ ቴራፒስት ታመነ ግርማ ይመክራሉ።
በቅብብሎሽ ወይም ከግል ጥቅም ጋር በተያያዘ በሌሎች መንገዶች የተቀበልናቸው እና ለእኛም ሆነ ለመጪው ትውልድ የማይጠቅሙ አመለካከቶችን እንደ አሮጌው ልብስ ከላያችን ላይ ማውለቅ ይጠበቅብናል ነው ያሉት።
ሐሳብ ይታደሳል ያሉት ባለሙያው፤ ያረጁ አሳሪ አስተሳሰቦችን በአዳዲስ ሀገርና ወቅቱ በሚፈልገው ሐሳብ በመተካት አዲሱን ዓመት መቀበል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
አዲሱን ዓመት ስንቀበል ለሀገር እና ለሕዝብ የሚጠቅም እሳቤን በመውለድ እንዲሁም የማይጠቅመውን በመተው ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ፋይዳ የለሽ አመለካከቶች የሚያደርሱትን ሥነ-ልቦናዊ ጫና በመገንዘብ ለሁሉም ተስፋ የሚሆን መልካም ሐሳብ መሰነቅ እንደሚገባ መክረዋል።
አንዱ ያለሌላው ምንም መሆኑን በተገነዘበ ሥነ-ልቦናዊ አካሄድ መጓዝ ይበጃል ያሉት ባለሙያው፤ ለሌሎች መኖርን፣ ወንድማማችነትን መላበስ ለጤናማ ኑሮ መሠረት መሆኑንም ይገልጻሉ።
በሌላ በኩል አዕምሮ አስተሳሰብ፣ ስሜት እና ባሕርይ በተሰኙ ሦስት መገለጫዎች እንደሚታወቅ አንስተው፤ የሦስቱ መገለጫዎች ሚዛናዊነት ከጎደለ የአዕምሮ እክሎችን እንደሚያመላክቱ ጠቁመዋል።
መፍትሔውን ሲገልጹም፤ በየቀኑ የሚረብሹና ለችግር የሚያጋልጡ ሁኔታዎች ካሉ ወደ አዲሱ ዓመት እንዳይሻገሩ ለማስወገድ መጣር ተገቢ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የሰው ልጅ መጀመሪያ በሆነ ነገር ራሱ ከተረበሸ ይህ መረበሽ ወደ ቤተሰብ ይጋባል፤ ከዚያም እየሰፋ ይሄዳል….ጉዳቱ ለሀገርም ሊተርፍ ይችላል። በትንሹ በሥራው ስኬታማ ካልሆነ በቤተሰብም ሆነ በሀገር ስኬታማነት ላይ አሉታዊ ሚና ያሳድራል።
ስለዚህ ያልተፈቱ የቤተሰብ፣ የማኅበራዊ ግንኙነት፣ የገንዘብ፣ የሥራና የሥራ ቦታ እንዲሁም ሌሎችም ችግሮች ካሉ ኪሳራቸው መልከ ብዙ ነውና ወደ አዲሱ ዓመት እንዳይቀጥሉ መፍትሔ ሊበጅላቸው ይገባል ነው ያሉት።
በአዲስ ዓመት ሰዎች ብዙ ነገሮችን ለማስተካከል የሚያቅዱበት በመሆኑ ይህ አጋጣሚ፤ በማብሰልሰል ውስጥን ለሚረብሹ ማኅበራዊ ችግሮች እልባት ለመስጠት የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ይናገራሉ።
በዚህም ልንፈታቸው (ልንቀይራቸው) የምንችላቸውን በመቀየር ወይም በመፍታት፣ መቀበል ያለብንን በመቀበል እና በጎ ትርጉም በመስጠት አዲስ ዓመትን መቀበል እንደሚገባ ነው የሚገልጹት።
የሀገር ግንባታ ከቤሰተብ ይጀምራል፤ በቤተሰብ ያለን ፍቅር ወደ ሌላው በማጋባት አዲስ ዓመትን ለሀገር የሚበጀውን መትከል የሚያስችሉ ፋይዳ ያላቸው በጎ ተግባራትን ለመፈጸም በመነሳሳት መቀበል እንደሚገባ ነው በኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል የተሃድሶ ሕክምና አስተባባሪ፣ ክሊኒካል ሳይኮሎጂስት እና የሳይኮሎጂካል ትራውማ ቴራፒስት ታመነ ግርማ የመከሩት።