ጉባኤው አፍሪካ ለዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ የመፍትሔ ማዕከል መሆኗን በግልጽ ያሳየ ነው - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
ጉባኤው አፍሪካ ለዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ የመፍትሔ ማዕከል መሆኗን በግልጽ ያሳየ ነው - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2017(ኢዜአ)፦ ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ አፍሪካ የመፍትሔና የታዳሽ ኃይል ማዕከል መሆኗን ያሳየችበት መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ፡፡
"ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማፋጠን፣ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ" በሚል መሪ ሀሳብ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የነበረው ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ዛሬ ተጠናቋል፡፡
ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በመዝጊያ መርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ አፍሪካ ግልጽ አቋሟን ያንጸባረቀችበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ተጎጂ ብቻ ሳይሆን በአረንጓዴ ልማትና በታዳሽ ሀይል ዓለም አቀፍ የመፍትሔ ማዕከል መሆኗን አሳይቷል ብለዋል፡፡
ዓላማችን የበለጸገች፣ አይበገሬና አረንጓዴ አፍሪካን መፍጠር ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የኤሌክትሪክ ሃይል የማያገኙ 600 ሚሊዮን አፍሪካውያን መኖራቸው ኢፍትሐዊነት መሆኑን የዓለም ማህበረሰብ ሊገነዘብ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን የመቋቋም ተግባራችን ያለንን ሰፊ ሀብት፣ የታዳሽ ሃይል ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ ፍትህ ላይ ማተኮር አለበት ብለዋል፡፡
በአፍሪካ ያለውን እምቅ የውሃና የጸሀይ ሀይል በመጠቀም ሁሉም ዜጎችና ድርጅቶች የኤሌክትሪክ ሃይል እንዲያገኙ ማድረግ እና በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
አፍሪካውያን በዓለም እንደ ተረጂ የምንታይበትን ትርክት በተባበረ አቅማችን መቀየርና የዓለም የመፍትሔ አካል መሆናችንን ማሳየት ይኖርብናል ብለዋል፡፡
አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ለዓለም የሚተርፍ መፍትሔ አላት ያሉት ፕሬዝዳንቱ ቢሊዮን ችግኞች በየዓመቱ የሚተከሉበት የአረንጓዴ ዐሻራ፣ የታዳሽ ኃይል ልማት፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።
የአዲስ አበባ የመሪዎች ቃል ኪዳን መጽደቅ ትልቅ እርምጃ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ በራሷ አቅም መፍትሔ እንደምታመጣ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የመሪዎች ቃል ኪዳን የታዳሽ ኃይልና የአረንጓዴ ልማትን በማስፋት ነገን መገንባት፣ ወሳኝ ማዕድናትን ጨምሮ የአህጉሪቱን የተፈጥሮ ሀብት በራስ ማስተዳደርና መጠቀም፣ ጥብቅ ደኖችን ጨምሮ የተፈጥሮ ቅርሶቻችንን መጠበቅ ላይ ያተኮሩ ሦስት ምሰሶዎች እንዳሉት አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ የመሪዎች ቃል ኪዳን በአጭር ጊዜ ዕቅድ ወጥቶለት ሊተገበር የሚገባ መሆኑንም አስገንዝበዋል።