ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ለአየር ንብረት ተስማሚ የሆነ ገበያ ተኮር የግብርና ፕሮግራም ይፋ አደረገች

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ምዕራፍ ለአየር ንብረት ተስማሚ የሆነ ገበያ ተኮር የኮታ ገጠም የግብርና ፕሮግራምን ይፋ አድርጋለች።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ(ዶ/ር)፥ መንግስት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ሥራ ቅድሚያ በመስጠት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ግብርና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትልቁ አንቀሳቃሽ መሆኑን ገልጸው በወጪ ንግድ እና የሀገር ውስጥ የምግብ ፍጆታን በማሟላት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

የመጀመሪያው ምዕራፍ ገበያ ተኮር የግብርና ፕሮግራም ትግበራ ከ4 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንዳደረገና በጥራጥሬ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ አመርቂ ውጤት እንደተመዘገበበት ተናግረዋል።

ሁለተኛው ምዕራፍ የተገኙ ስኬቶችን ማስቀጠል በሚቻልበት መንገድ መዘጋጀቱን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሤ(ዶ/ር) ፕሮግራሙ በርካታ ግቦች እንዳሉት ጠቅሰዋል።

ፕሮግራሙ ኢትዮጵያ አነስተኛ የእርሻ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም እርሻ ተጠቃሚ የሚያደርግ ለአየር ንብረት ተስማሚ የሆነ ገበያ ተኮር ግብርናን ለማሳደግ ያላትን ጠንካራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ፕሮግራሙ ግብርና የምግብ ዋስትና እና የኢኮኖሚ ለውጥ አንቀሳቃሽ የመሆን አቅሙን ለማጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጨምረዋል።


 

በዴንማርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የልማት ፖሊሲ ምክትል ጸሐፊ ኦሌ ቶንኬ የዴንማርክ መንግስት ለኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ የ75 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

ዴንማርክ ለኢኮኖሚ እድገት እና ለሥራ ፈጠራ አስፈላጊ በሆነው የግብርና ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር በመስራቷና የልማት አጋር በመሆኗ ኩራት እንደሚሰማትም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም