ሦስተኛው በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ዕቅድ የአረንጓዴ ልማት ግቦችን የሚያሳካ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሦስተኛው በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ዕቅድ የአረንጓዴ ልማት ግቦችን የሚያሳካ ነው

አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 5/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሦስተኛው በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ብሔራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ የ10 ዓመት ዕቅድ የአረንጓዴ ልማት ግቦችን የሚያሳካ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን ገለጹ፡፡
ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ የሦስተኛ ቀን ውሎ የውይይት መድረክ ዛሬም በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ተካሂዷል።
የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ በግብርና፣ የአፈር ማዳበሪያ፣ ታዳሽ ሀይል፣ የአየር ንብረት ፋይናንስ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት የሚያስችሉ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት የበካይ ጋዝ ልቀትን በመቀነስ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም ሶስተኛውን በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ የ10 ዓመት ዕቅድ ይፋ አድርጓል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን ዕቅዱን ይፋ ባደረጉበት ወቅት፤ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ዕቅድ በፓሪስ ስምምነት መሰረት በየአምስት ዓመቱ ማሻሻያ እንደሚደረግበት አውስተዋል።
ኢትዮጵያም እ.አ.አ ከ2025 እስከ 2035 የሚተገበር ሦስተኛውን በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ብሔራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ዕቅድ ማውጣቷን ገልጸዋል።
ዕቅዱ ከኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ ከሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ ከ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ እና ከረጅም ጊዜ የካርበን ልቀት ስትራቴጂክ ዕቅድ ጋር የተጣጣመ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አማካይነት የደን ሽፋን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልጸው፤ በ2030 ወደ 30 በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል ብለዋል።
የአስር ዓመቱ ዕቅድ የግብርና ምርታማነትን፣ የከተማ መሰረተ ልማትን፣ የታዳሽ ኃይል አቅርቦትን እና የሰብል ምርታማነትን ተጨባጭ በሆነ መንገድ የሚያሳድግ ነው ብለዋል።
በዶሮ እርባታ፣ በንብ ማነብ፣ በስጋ ምርት እንዲሁም በመስኖ ልማትና በሌሎች የግብርና ዘርፎች የተመዘገቡ ለውጦችን ማስቀጠል እንደሚችልም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ለብዝኃ ህይወትና ሥርዓተ ምህዳር ጥበቃ፣ የመሬት መሸርሸርን ለመከላከል ጠንካራና ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚ ለመገንባት በጀት መድባ እየሰራች ነው ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ይጠይቃል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ብሔራዊ ዕቅዱን ለማሳካት 98 ነጥብ 35 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ለዕቅዱ መሳካት ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ በፋይናንስ፣ በቴክኒክ እና በቴክኖሎጂ ዕገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በዓለም ባንክ የምሥራቅ አፍሪካ የአካባቢ ዘርፍ ማናጀር ፖል ማርቲን፤ ባንኩ በኢትዮጵያ ለዘላቂ ደን እና መሬት ልማት አስተዳደር ቅድሚያ በመስጠት በትብበር መስራቱን ገልጸዋል፡፡
በዚህም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መቋቋም የሚያስችል የአፈርና ውሀ ጥበቃ እንዲሁም የተራቆተ መሬት ማገገም ላይ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል፡፡
የዓለም ሪሶርስ ኢንስቲትዩት ግሎባል ዳይሬክተር ሜላኒ ሮብሰን የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ፣ የኤሌክትሪክ ትራንስፖርት ስርዓትና ሌሎችም ኢኒሼቲቮች የአረንጓዴ ልማትን የሚደግፉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን በራሷ አቅም መቋቋም የሚያስችል እምቅ አቅም እንዳላት ያነሱትን ሀሳብ የኢትዮጵያ ኢኒሼቲቮች አረጋግጠዋል ነው ያሉት።
የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ አጋርነት ዓለም አቀፍ ዳይሬክተር ፓብሎ ቬራ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም የምታደርገውን ጥረት አድንቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ዕቅድ ትግበራ ያስመዘገበችው ስኬት በቀጣናውና በዓለም መሪ ያደርጋታል ብለዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም የኢትዮጵያን ድንቅ ሥራዎች በሌሎችም ሀገራት መድገም እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሦስተኛውን በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ብሔራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ዕቅድ እንድታሳካ ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል።