አዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለህብረተሰቡ ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለህብረተሰቡ ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 5/2017(ኢዜአ)፦አዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለህብረተሰቡ ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በመረቅን ማግስት የህዝብን እንግልት የሚቀንስ የአዲስ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል ብለዋል፡፡
አዲስ መሶብ የተገልጋዮችን እንግልት በመቀነስ ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት እና ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ ቀን ከሌሊት ህዝብን በብዙ መንገድ ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
በርካታ የከተማዋን ገጽታ የመቀየር ስራዎች መሰራታቸውንና ሰው ተኮር የልማት ስራዎችን በማከናወን የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በዛሬው እለት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት በሆነው የአዲስ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት አሁን ላይ 13 ተቋማት መካተታቸውን ገልጸዋል፡፡
የእነዚህ ተቋማት 107 የሚሆኑ አገልግሎቶች በዲጂታል አማካኝነት ለተገልጋዮች ተደራሽ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡
በዛሬው እለት የተመረቀው የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከል ለህዝባችን በአዲስ ዓመት ያቀረብነው ስጦታ ነው ብለዋል፡፡
በሁሉም ክፍለ ከተሞች የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲኖር በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት በከተማዋ የዲጂታል አሰራርን ለማስፋት በተሰሩ ስራዎች ውጤቶች መመዝገባቸውን የጠቆሙት ከንቲባዋ፤ ይህ ስራ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡