ቀጥታ፡

በሁሉም መስክ የተሻለ ነገን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የድርሻችንን መወጣት አለብን -ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል 

አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 5/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ በሁሉም መስክ የተሻለ ነገን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የድርሻችንን መወጣት አለብን ሲሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።   

ጳጉሜን 5 የነገው ቀን ''ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ማድረግ'' በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ መርኃ ግብሮች ተከብሯል።


 

በመርሃግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፥ ኢትዮጵያ ወደ ትክክለኛ ከፍታዋ ለመሻገር እየሰራች ነው ብለዋል።

እንደ ሀገር ከትናንት የተሻለ ዛሬንና ከዛሬ የተሻለ ነገን እየገነባን ነው ያሉት ሚኒስትሯ ይህን አጠናክሮ ለመቀጠል ብቃት ያለው የሰው ሃይልና የቴክኖሎጂ መዘመን ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያን ነገን የተሻለ ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራትን ለማሳካት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እና ኢኖቬሽን የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ፣ አይበገሬነትን ለማጽናት እና የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ ወሳኝ ናቸው ብለዋል።


 

ትናንት የተመረቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ታላቅ የለውጥ ማሳያ እንደሆነ ተናግረው፤  አዲስ የከፍታ ምዕራፍ መጀመሪያ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዲጂታል የጎለበተች፣ የምግብ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠች እና ለችግሮች የማትበገር ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ሁላችንም የበኩላችንን መወጣት አለብን ብለዋል።

ነገዋን  በራሷ የምትፈጥር ኢትዮጵያን እንገንባ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም