ቀጥታ፡

ለአየር ንብረት ተስማሚ አረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማስፋፋት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 5/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ዘመናዊና ለአየር ንብረት ተስማሚ አረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማስፋፋት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)ገለጹ።

የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከ'ኮይፓ ኢታሊያ' ከተሰኘ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር ስትራቴጂክ ስምምነት አድርገዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ የባቡር መሰረተ ልማቶች ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ማዕከል ናቸው።

መሰረተ ልማቶቹ ወጪን ይቀንሳሉ፣ የገበያ ትስስር ይፈጥራሉ፣ የስራ እድል ያስፋፋሉ፣ አረንጓዴ የኢኮኖሚ ልማትን ይደግፋሉ ብለዋል።


 

ዛሬ የተደረገው ስምምነት የስራ አጋርነት ብቻ ሳይሆን የሁለቱን አገራት ወዳጅነት የሚያሳይ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ዘመናዊና ዘላቂነት ያለው የባቡር ትራንስፖርት ለማስፋፋት የሚያግዝ መሆኑን ገልጸው፤  ዘመናዊና ለአየር ንብረት ተስማሚ አረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማስፋፋት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ በባቡር ዘርፍ የያዘችውን ራዕይ ለመደገፍ ጣሊያን ላሳየችው ቁርጠኝነት አመስግነው፤ ኢትዮጵያ በዘርፉ  ከጣሊያን ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።


 

በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር አጉሰቲኖ ፓልሴ(ዶ/ር)፤ ከኢትዮጵያ ጋር ያለን ወዳጅነት እንዲሁም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነትን ለማሻሻል እንደሚሰራ ገልጸዋል።


 

በባቡር ዘርፍ ያለንን የዳበረ ልምድ በማካፈል ከኢትዮጵያ  ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ ነን ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም