በሁሉም የምርት ዓይነቶች በቂ አቅርቦት በመኖሩ በዓሉን በደስታ ለማሳለፍ ተዘጋጅተናል- የወልዲያ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በሁሉም የምርት ዓይነቶች በቂ አቅርቦት በመኖሩ በዓሉን በደስታ ለማሳለፍ ተዘጋጅተናል- የወልዲያ ነዋሪዎች
ወልዲያ፤ ጳጉሜን 5/2017(ኢዜአ)፦ለዘመን መለወጫ በዓል በሁሉም የምርት ዓይነቶች በቂ አቅርቦት በመኖሩ በዓሉን በአቅማቸው ልክ ሸምተው በደስታ ለማሳለፍ መዘጋጀታቸውን በወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ዘውዱ መንገሻ እንዳሉት፤ በበዓል ዋዜማ ገበያ ያለው አቅርቦት ካለፉት ጊዜያት የተሻለና ገበያውም የተረጋጋ ነው።
በእንስሳትና በእንስሳት ተዋጽኦ ላይ መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ ቢኖርም በየምርቱ ዓይነት በቂ አቅርቦት በመኖሩ በአቅማቸው ልክ አመቻችተው በዓሉን በደስታ ለማሳለፍ መሰናዳታቸውን ገልጸዋል።
የዘንድሮው የአዲስ ዓመት በዓል ልዩ የሚያደርገው የሁላችንም ሃብት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተመረቀበት ማግስት የሚከበር በመሆኑ ነው ብለዋል።
ወይዘሮ ሸዋዬ ዓለሙ በበኩላቸው፤ ዘይት፣ ዱቄት፣ ስኳርና ሌሎች የእህል ምርቶች በህብረት ስራ ማህበራት እየቀረቡ በመሆኑ በተመጣጣኝ ዋጋ በመግዛት በዓሉን በደስታ ለማሳለፍ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
መንግስት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እያደረገ ያለውን ጥረት አሁንም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል።
የከተማው ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አዲሱ ወንድሙ በበኩላቸው ፤ የበዓሉ መምጣትን ተከትሎ የሚደረግ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪን ለመቆጣጠር ከክፍለ ከተሞችና ቀበሌዎች ጋር ቅንጅት በመፍጠር ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
በከተማው መደበኛ ቦታዎች በተጨማሪ በዓሉን አስመልክቶ አራት ተጨማሪ የመገበያያ ቦታዎች ተመቻችተው ሕዝቡ በአቅራቢያው እየተገበያየ ነው ብለዋል።
ዘይትና ዱቄት በሕብረት ስራ ማህበራት በኩል የቀረበ ሲሆን ፤ ከነጋዴ በእጥፍ ያህል የቀነሰ ሶስት ሊትር ዘይት በ450 ብር በቅናሽ ዋጋ እየተሸጠ መሆኑንም አንስተዋል።