አዲሱ ዓመት ሰላም የሚጸናበት እና የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በስኬት የሚጠናቀቁበት ይሆናል - የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ ዓመት ሰላም የሚጸናበት እና የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በስኬት የሚጠናቀቁበት ይሆናል - የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ
አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 5/2017(ኢዜአ)፦አዲሱ ዓመት ሰላም የሚጸናበት እና የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በስኬት የሚጠናቀቁበት እንደሚሆን የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ገለጹ፡፡
የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ የ2018 ዓ.ም አዲስ ዓመትን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፤ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ለጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊት እንኳን ለ2018 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል፡፡
አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት እና የስኬት እንዲሆን ተመኝተዋል።
2018 ዓ.ም በመላው አገራችን ሰላም በተሟላ መንገድ የሚሰፍንበት እና የተጀመሩ ስራዎች በስኬት የሚጠናቀቁበት ይሆናል ነው ያሉት፡፡
ያለፈው ዓመት ጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊት የአገሩን ዳር ድንበር በማስጠበቅ ረገድ ውጤታማ ስራዎችን ያከናወነበት እንደነበር ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም ይህን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረው፤ አመራሩም በዚህ ረገድ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ኢትዮጵያን የሚመጥናት ከፍታ ላይ እንድትደርስ እየተጋ ካለው ጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በመሆን የተለመደ አጋርነቱን እንዲያሳይ አደራ ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ አገርን እየፈተኑ የሚገኙ የውስጥ ባንዳዎችን ነቅሶ በማውጣትና መክሮ ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጡ በማድረግ ረገድም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡