ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ሀዋሳ፤ ጳጉሜን 5/2017(ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል በቴክኖሎጂ የተደገፈ ከወረቀት ነጻ አገልግሎት በመስጠት እንደ ሀገር ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ።
“ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ማድረግ” በሚል መሪ ሀሳብ የነገው ቀን በሲዳማ ክልል ደረጃ በሀዋሳ ተከብሯል።
የሲዳማ ክልል መንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ አስፋው ጎኔሶ በመርሀግብሩ ላይ እንዳሉት በክልሉ የሚሰጠውን አገልግሎት ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው።
በክልሉ በሀዋሳ የአንድ መሶብ አገልግሎትን ለማስጀመር የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።
ለዚህም በርካታ ተገልጋይ ያላቸው አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ተመርጠውና ለስራ ምቹ የሚሆን ህንጻ ተዘጋጅቶ የኔትወርክ ዝርጋታ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአንድ መሶብ አገልግሎቱ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የሚሰጥበት ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ጠቁመዋል።
የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ሀላፊ አቶ አሰፋ ጉራቻ በበኩላቸው እንደገለጹት በክልሉ በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ ከወረቀት ነጻ የሆነ አገልግሎት በመስጠት የተገልጋዩን እርካታ ለማምጣት በትኩረት እየተሰራ ነው።
ህብረተሰቡ ለእንግልት የሚዳረግባቸውን አገልግሎቶች በመለየት በአንድ ማዕከል ውስጥ ያለ ውጣውረድ በኦን ላይን ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል ።
የመሶብ አገልግሎቱ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውና ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎችን እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።
የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተፈራ በራሶ የዲጂታል አገልግሎቱን በተሳካ ሁኔታ ለማስጀመር እንዲቻል የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕውቀት ያለው ትውልድ መፍጠር ዋና ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም በኮደርስ ኢትዮጵያ እስካሁን ከ30 ሺህ በላይ የክልሉ ነዋሪዎች ስልጠና እንዳገኙ ጠቁመው እንደ ሀገር ዲጂታል ኢኮኖሚን ለማሳካት በክልሉ ቢያንስ 50 በመቶ የመንግስት ሰራተኛው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕውቀት እንዲኖረው ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አስታውቀዋል።
“ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ማድረግ” በሚል መሪ ሀሳብ በተከበረው የነገው ቀን በዓል ላይ በክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ተጠሪ የሆኑ ተቋማትና ኤጀንሲዎች ሰራተኞች ተገኝተዋል።