ቀጥታ፡

በአዲሱ ዓመት የላቁ ሀገራዊ ስኬቶችን ለማስመዝገብ መትጋት ይገባል - የሃይማኖት አባቶች

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2017(ኢዜአ)፦ በአዲሱ ዓመት የላቁ ሀገራዊ ስኬቶችን ለማስመዝገብና ሠላምና አብሮነትን ለማጠናከር መትጋት እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ገለጹ።

የሃይማኖት አባቶች ለ2018 አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አዲሱን ዓመት አስመልክተው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፥ አዲሱን ዓመት ስናከብር ለሀገር ሰላምና ልማት እንዲሁም አንድነትን ለማጠናከር መትጋት ይገባል ብለዋል።

አዲሱ ዓመት የላቁ ሀገራዊ ስኬቶች የሚመዘገቡበት እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት የሃይማኖት አባቶችና መላው ህብረተሰብ በጋራ መትጋትና መጸለይ እንደሚገባም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ብፁዕ አቡነ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል፥ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መመረቁ ለኢትዮጵያውያን የብርሃንና የስኬት ዘመን መጀመሩን የሚያበስር ነው ብለዋል።

አዲሱ ዓመት ለሀገርና ለህዝብ በጎ ነገሮችን እንድንከውን የተሰጠን ጸጋ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

አዲሱን ዓመት የተቸገሩ ወገኖችን ማገዝና መጠየቅ እንደሚገባም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ጸሐፊ ቄስ ደረጄ ጀምበሩ እንዳሉት፤ በተጠናቀቀው ዓመት እንደ ሀገር የላቁ ድሎች የተመዘገቡበት እንደሆነም አንስተዋል።

የ2018 አዲስ ዓመትን የምንቀበለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ ለሀገራችን አዲስ ብስራት በታወጀበት ወቅት መሆኑም ትልቅ መነሳሳትን የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በአዲሱ ዓመት ትውልዱ ለሀገሩ በታማኝነትና በትጋት በመሥራት፣ እውቀትና ጉልበቱን ተጠቅሞ የላቀ ለውጥ ለማስመዝገብ እንዲሠራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም