በአዲሱ ዓመት ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ሰላምን የማጽናት ስራዎቹን አጠናክሮ ይቀጥላል - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲሱ ዓመት ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ሰላምን የማጽናት ስራዎቹን አጠናክሮ ይቀጥላል - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2017(ኢዜአ)፡- በአዲሱ ዓመት ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ሰላምን የማጽናት ስራዎቹን አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የ2018 አዲስ ዓመትን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ በግዳጅ ለሚገኘው ለጀግናው የአገር መከላከያ ሠራዊት እንኳን ለዘመን መለወጫ በዓል አደረሳችሁ ብለዋል፡፡
2017 ዓ.ም ጀግናው የአገር መከላከያ ሠራዊት የተሰጠውን ተልዕኮ በድል የተወጣበት ዓመት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም 2017 ዓ.ም የተሻለ የሰላም ድባብ የታየበት ዓመት ሆኖ እንዳለፈም አመልክተዋል፡፡
መከላከያ ሠራዊት የአገር ሉዓላዊነት የመጨረሻ ምሽግ ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ ይህንንም በተግባር ማሳየቱን አስታውቀዋል፡፡
ለዚህም ከፍተኛ ክብርና ምስጋና አለኝ ነው ያሉት፡፡
2018 ዓ.ም የተጀመሩ ስራዎች የሚጠናቀቁበት እና ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ ተፈተው ሀገራችን ወደ ተሟላ ሰላም የምትሸጋገርበት ዘመን ይሆናል ብለዋል፡፡