ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን በዲጅታል ቴክኖሎጂ በማስደገፍ ፈጣንና ቀልጣፋ እንዲሆን እየተደረገ ነው

አዳማ፤ ጳጉሜን 5/2017(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል የመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን በዲጅታል ቴክኖሎጂ በማስደገፍ ፈጣንና ቀልጣፋ እንዲሆን እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።

በዛሬው የ"ነገው ቀን" መርሃ ግብር "ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ማድረግ" በሚል መሪ ሀሳብ የአዳማ ከተማ አስተዳደር የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን አስጀምሯል።

በከተማ አስተዳደሩ አገልግሎቱን ያስጀመሩት በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ከፍያለው ተፈራ፣ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) እና የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኃይሉ ጀልዴ ናቸው።


 

በዚህ ወቅት በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ከፍያለው ተፈራ እንደገለጹት፤ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ በማሻሻል መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ለዲጂታል ኢትዮጵያ እውን መሆን ወሳኝ ነው።

ዲጂታል ኢትዮጵያ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን በመተግበር ግልጸኝነትንና ተጠያቂነትን መዘርጋት ትኩረት እንደተሰጠው ተናግረዋል።

በዛሬው እለት አገልግሎቱ አዳማን ጨምሮ በቢሾፍቱ፣ ሸገር እና ሻሸመኔ ከተሞች መጀመሩን አስታውቀዋል።

በቀጣይም በሁለተኛው ምዕራፍ በበርካታ ከተሞች አገልግሎቱን ማስፋት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም ከመንግስት አገልግሎት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችንና መልካም አስተዳደርን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ገንቢ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።

የክልሉ መንግሥት የሕብረተሰቡን ጥያቄ በቅርበት ለመፍታትና የአገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ ለማሻሻል በ5ሺህ ቀበሌዎች ሰራተኞችን በመመደብ አርሶ አደሩ ከቀዬው ሳይርቅ አገልግሎት እያገኘ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት እንቅስቃሴዎችን በማሳለጥ የክልሉ ብሎም የሀገር መንሰራራትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በርካታ ተቋማት ቴክኖሎጂ በመጠቀም አገልግሎታቸውን በማዘመን ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በአዳማ ዛሬ የተጀመረው የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ በዲጅታል ቴክኖሎጂ የተደገፈ ፈጣንና ቀልጣፋ እንዲሆን እንደሚያስችል አነስተዋል።

አገልግሎቱ አስተማማኝና የተሳለጠ እንዲሆን የሰው ኃይልን ለማብቃት ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራም አንስተዋል።


 

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው፤ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በአስተዳደሩ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ በማድረግ ሙሉ በሙሉ መቀየር ማስቻሉን ተናግረዋል።

በዚህም የመሬት አስተዳደር፣ ኢንቨስትመንት፣ ኮንስትራክሽንን ጨምሮ ከ100 በላይ አገልግሎቶችን በተቀላጠፈ መንገድ ለተገልጋዩ ሕብረተሰብ መስጠት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ይህም የተገልጋዩን እርካታ እና የከተማዋን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ ወሳኝነት እንዳለው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም