ቀጥታ፡

በክልሉ በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት አሰጣጥን በማስፋት ለመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ይሰራል

ቦንጋ፤ ጳጉሜን 5/2017(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት አሰጣጥን በማስፋት ለህዝቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ የመስጠቱ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የጳጉሜን 5 'የነገው ቀን' "ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ማድረግ" በሚል መሪ ሃሳብ በቦንጋ ከተማ ተከብሯል።



የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አስራት አዳሮ በዚህ ጊዜ እንደተናገሩት የመንግስት አገልግሎትን ለማዘመን በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሰራሮች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።

አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን ከአድሎ የፀዳ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የአንድ ማዕከል አገልግሎት በክልሉ በአምስት ተቋማት 15 አገልግሎቶችን ለማስጀመር ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸዋል።

ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የኮደርስ ስልጠናም በክልሉ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል፡፡




የክልሉ ዋና ኦዲተር አስራት አበበ በበኩላቸው የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ መዘመን ከኪራይ ሰብሳቢነት የፀዳ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎትን ለመስጠት የሚያግዝ በመሆኑ ተቋማት ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የፌደራል መንግስት ያመቻቸው የ5 ሚሊዮን ኮደርስ ስልጠና አለም አቀፍ እውቅና ያለው ትልቅ እድል በመሆኑ በተገቢው መጠቀም ይገባል ብለዋል።

የነገዋን ኢትዮጵያ የተሻለች ለማድረግ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እንዳሻው ከበደ ናቸው፡፡

በዞኑ ፍርድ ቤት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ የማድረግ ጅምር ስራዎች መኖራቸውን ጠቁመው በሌሎች ተቋማትም ይጠናከራሉ ብለዋል፡፡

በመድረኩ የክልል፣ የዞንና የቦንጋ ከተማ አመራሮችና የመንግስት ሰራተኞች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም