በደሴ ከተማ አገልግሎት አሰጣጥን ዲጂታላይዝድ የማድረግ ጥረቱ ውጤት እያስመዘገበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደሴ ከተማ አገልግሎት አሰጣጥን ዲጂታላይዝድ የማድረግ ጥረቱ ውጤት እያስመዘገበ ነው

ደሴ ፤ጳጉሜን 5/2017(ኢዜአ)፦በደሴ ከተማ አስተዳደር ለህዝብ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝድ የማድረግ ጥረቱ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑ ተገለፀ።
ጳጉሜን 5 የነገ ቀን "ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ማድረግ" በሚል መሪ ሃሳብ በደሴ ከተማ በፓናል ውይይትና በሌሎችም ዝግጅቶች ተከብሯል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የደሴ ከተማ አስተዳደር ማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰይድ የሱፍ እንደገለጹት፣ ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት እየተሰራ ነው።
በዚህም በከተማ አስተዳደሩ ቴክኖሎጂን በማስፋፋት አገልግሎቱን ዲጂታላይዝድ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ውጤት በማስመዝገባቸው ተጠናክረው ቀጥለዋል ብለዋል።
በተለይ ስማርት ሲቲን ጨምሮ የገቢ ግብር አሰባሰብ፣ ስራና ስልጠና፣ መሬት፣ ከተማ ልማት፣ ንግድና ሌሎችንም አሰራሮች በቴክኖሎጂ በማስደገፍ አገልግሎቱን ከማፋጠን ባለፈ ብልሹ አሰራሮችን ማስቀረት መቻሉን ጠቁመዋል።
በዚህም ቴክኖሎጂን የተላመደ ትውልድ ከመፍጠር ባለፈ የከተማውን ቀጣይ እድገት ታሳቢ ያደረጉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ቡድን መሪ ወይዘሮ ትዝታ ወንድሙ በበኩላቸው በከተማው የተለያዩ ተቋማትን ዲጂታላይዝድ በማድረግ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ከወረቀት ንክኪ ነጻ አገልግሎት በመስጠት ህብረተሰቡ ጊዜውን፣ ጉልበቱንና ገንዘቡን እንዲቆጥብ ከማድረግ ባለፈ ብልሹ አሰራሮችንም ማስቀረት ተችሏል ብለዋል።
አገልግሎቱን ዲጂታል ማድረግ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከማስቀረት ባለፈ ፍትሃዊ አገልግሎት መስጠት ተችሏል ያሉት ደግሞ በከተማው ገቢዎች መምሪያ የመረጃ ቴክኖሎጂ ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሀይለስላሴ አምባቸው ናቸው።
የግብር አሰባሰብ ሂደቱንም ዲጂታላይዝድ በማድረግ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ማስቀረት መቻሉን ጠቁመው ማጭበርበርና ሌሎች የዘርፉን ተግዳሮቶችንም መከላከል ተችሏል ብለዋል።
ኢ-ታክስ የሚባል ቴክኖሎጂ በማበልጸግ ግብር ከፋዮች ባሉበት ስፍራ ሆነው ግብር መክፈልና የንግድ ፍቃዳቸውንም ማደስ እንደሚችሉም አመልክተዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይም አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን ለ1 ሺህ 200 ባለይዞታዎችም የዲጂታል ካርታ ሰርተፊኬት ተሰጥቷቸዋል።