በክልሉ በጤናው ዘርፍ የዲጅታል አገልግሎትን በማስፋት የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በጤናው ዘርፍ የዲጅታል አገልግሎትን በማስፋት የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ እየተደረገ ነው

ጅግጅጋ፤ጳጉሜን 5 /2017(ኢዜአ) ፡-በሶማሌ ክልል በጤናው ዘርፍ የዲጅታል አገልግሎትን በማስፋት የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ።
ጳጉሜን 5 "የነገ ቀን" ''ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ማድረግ'' በሚል መሪ ሀሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ በመከበር ላይ ይገኛል።
እለቱ በሶማሌ ክልል በውይይትና ሌሎችም መርሃ ግብሮች የተከበረ ሲሆን የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሙሴ አህመድ፤ በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት ባደረጉት ንግግር ለድጅታል ልማት ስራዎች በክልሉ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ የኮደርስ ስልጠናን ጀምሮ ሌሎችም የዲጅታላይዜሽን ማጠናከሪያ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተው በጤናው ዘርፍ የዲጅታል አገልግሎትን በማስፋት የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ከጤናው ዘርፍ ባለፈም በሌሎች መስኮች የዲጅታል አሰራርን በማስፋት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት የመስጠትና አሰራሮችን የማዘመን ጥረቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
በክልሉ የቱሪዝም፣ የግብርና፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትና ሌሎችም መስኮች የልማት ስራዎች እየተሳለጡ ስለመሆኑም ዶክተር ሙሴ አንስተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን በዲጂታል ዘርፉ የተከናወኑ ዋና ዋና ስራዎችን የሚያመላክቱ ስራዎች ለእይታ ቀርበዋል።
በእለቱ በዲጂታል አተገባበር የላቀ አፈጻጸም ላሳዩ ተቋማትም እውቅና ተሰጥቷቸዋል።