በጅማ ከተማ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጅማ ከተማ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው

ጅማ፣ጳጉሜን 5/2017(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።
በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ሳዳት ነሻ፤ በጅማ ከተማ በመገኘት ለአገልገሎቱ የተዘጋጀውን ህንፃ መርቀዋል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር፣ በክልሉ የዲጂታል አሰራርን በማስፋት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት የማመቻቸት ተግባር ትኩረት እንደተሰጠው ተናግረዋል።
በዚህም በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ በጅማ ከተማም ለዚሁ አገልግሎት የሚሰጥ ህንፃ ዝግጁ መሆኑን አንስተዋል።
በክልሉ የአገልግሎት አሰጣጥን የሚያሳልጥ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመጀመር ዝግጅት መደረጉን ጠቁመው፤ ለዜጎች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት የመስጠት ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
የጅማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ጣሃ ቀመር፤ የጅማ ከተማን የአገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን የላቀ አገልግሎት መስጠትና ከተማዋን ስማርት የማድረግ ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በዛሬው እለት ለምረቃ የበቃው ህንፃም በከተማዋ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
የጅማ ከተማ ሲቪል ሰርቪስ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አብዶ አባጊዲ፤ በከተማዋ በተዘጋጀው ዘመናዊ ህንፃ 123 አገልግሎቶችን በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።