ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል የዲጂታል ኢኮኖሚ የልማት ዘርፉን በማጠናከር የህዝቡ ተጠቃሚነት ይሻሻላል

ጋምቤላ፤ ጳጉሜን 5/2017 (ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል የዲጂታል ኢኮኖሚ የልማት ዘርፉን በማጠናከር የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሻሻል የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀል የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጳጉሜ 5 የነገው ቀን ‹‹ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ማድረግ›› በሚል መሪ ቃል በጋምቤላ በፓናል ውይይትና በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሮ ውሏል፡፡


 

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ዕለቱን አስመልክተው እንዳሉት በክልሉ ዲጂታል ቴክኖሎጂን በማስፋት ህዝቡን በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ የልማት ዘርፎች ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

እንደ ሀገር ለውጥ ከተደረገባቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሞች መካከል የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ አንዱ መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡

በመሆኑም የዲጂታል ቴክኖሎጂው የማክሮ ኢኮኖሚውን በማስተካከልና መዋቅራዊ ችግሩን በመፍታት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

በተለይም ዜጎች በዲጂታል የቴክኖሎጂ ምህዳሩ የሚጠበቅባቸውን ሚና መጫወት እንዲችሉ ከመደበኛው መርሃ ግብሮች በተጨማሪ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለው የኮደርስ ነጻ የቴክኖሎጂ ስልጠና ተመቻችቶ በርካታ ዜጎች የእድሉ ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም እንደ ሀገር እየተተገበረ ያለውን የዲጂታል ኢኮኖሚውን በክልሉም እውን ለማድረግ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል የማፍራቱ ሂደት ተጠናከሮ እንደሚቀጥል ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ገልጸዋል። 

የክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሯች ባየክ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በተከናወኑ ስራዎች ጉልህ ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል፡፡

ዲጂታል ቴክኖሎጂው ክህሎት መር የስራ እድል ፈጠራን ለማጠናከር እየተከናወነ ያለውን ተግባር በማሳለጥ በኩል የማይተካ ሚና እየተጫመተ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም