ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል በዲጂታል ቴክኖሎጂ ትግበራ የሚከናወኑ ተግባራት ይጠናከራሉ

ሐረር ፤ዻጉሜ 5/2017 (ኢዜአ)፡-  በሐረሪ ክልል በዲጂታል ቴክኖሎጂ ትግበራ የሚከናወኑ  ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ገለጸ።

በክልሉ ‘ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ማድረግ' በሚል መሪ ሃሳብ ጳጉሜን 5 “የነገው ቀን” በፓናል ውይይት ተከብሯል።

በከተማው በሚገኘው አሚር አብዱላሂ መሰብሰቢያ አዳራሽ በተከናወነው የፓናል ውይይት የሐረሪ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ጀማል ኢብራሂም የመወያያ ጽሁፍ አቅርበዋል።


 

በወቅቱም እንዳሉት በክልሉ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ትግበራ ውጤታማ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል። 

በተለይ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የአገልግሎት አሰጣጥ ስራዎች በተለያዩ ሴክተር ተቋማት እየተከናወኑ ስለመሆኑም አንስተዋል።

ከክልሉ ቴክኒክና ሙያ ኤጀንሲ ጋር በመሆን ክህሎትን ከማበልጸግ አኳያ የሚከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በክልሉ እስካሁን ከ14 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶችና ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና መሰጠቱ ገልጸዋል።

ስልጠናውን ከወሰዱት መካከል ከ8 ሺህ በላይ ለሚሆኑት የእውቅና የምስክር ወረቀት መሰጠቱንም ተናግረዋል።

የሚሰጡ አገልግሎቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ወደ ተሻለ ደረጃ የማድረስ ስራ በትኩረት መስራት ይገባል ያሉት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጃፈር ሱፍያን ናቸው።

ይህም የተቋምን የመፈጸም አቅም በማጎልበትና የአሰራር ስርዓትን ቀልጣፋ በማድረግ ህዝቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኝ ያስችላል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይም የሐረሪ ክልል ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አሚና አብዱልከሪምን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ተማሪዎችና ሌሎች የተሳተፉ ሲሆን በእለቱም በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ለወሰዱ የምስክር ወረቀት ተበርክቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም