ቀጥታ፡

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተቀላጠፈ አሰራርን በመከተል የተጋልጋዮችን አመኔታ ያሳድጋል

አሶሳ፤ጳጉሜን 5/2017 (ኢዜአ)፦መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተቀላጠፈ አሰራርን በመከተል የተገልጋዮችን አመኔታ የሚያሳድግ መሆኑን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) ተናገሩ።

ኮሚሽነሩ ጳጉሜ 5 የነገው ቀን አከባበር ላይ በአሶሳ ከተማ የተገነባውን ቤጉ የመሶብ አገልግሎት መስጫ ማዕከል መርቀው ከፍተዋል።

የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ(ዶ/ር) በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ዜጎች ከመንግስት የሚያገኙትን መሠረታዊ አገልግሎቶችን የማዘመን ስራ በትኩረት እየተከናወነ ነው።


 

በተቋማት የሚታየውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለመፍታት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አንዱ መፍትሔ መሆኑን ተናግረዋል።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዜጎች በክብርና በቅልጥፍና እንዲያስተናገዱ እና በተቋማት ላይ አመኔታ እንዲኖራቸው ያደርጋል ነው ያሉት።

የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ ፍትሐዊ እና ተጠያቂነት የሚያሰፍን ሆኖ ከንክኪ የፀዳ በመሆኑ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል።

በሁሉም አካባቢዎች የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በማስፋፋት የተቀላጠፈ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ለመፍጠር እየተሰራ ነው ብለዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው፥መሶብ የአንድ ማዕከል የአገልግሎት ማዕከል ለተያዘው የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ አጋዥ እንደሆነ አብራርተዋል።


 

አገልግሎቱ ዜጎችን ከአላስፈላጊ ወጪ የሚታደግ እና እርካታን የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ቤጉ የመሶብ አገልግሎት ማዕከል በክልሉ በስምንት የክልል እና የፌዴራል ተቋማት አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር የገለፁት ደግሞ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታሁን አብዲሳ ናቸው።


 

ከየተቋማቱ ባለሙያዎች ተመድበው አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም