ኢትዮጵያውያን በቀላሉ የፋይዳ ዲጂታል ብሔራዊ መታወቂያ ባለቤት የሚሆኑበት ምኅዳር ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን በቀላሉ የፋይዳ ዲጂታል ብሔራዊ መታወቂያ ባለቤት የሚሆኑበት ምኅዳር ተፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 5/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያውያን በቀላሉ የፋይዳ ዲጂታል ብሔራዊ መታወቂያ ባለቤት የሚሆኑበት ምኅዳር መፈጠሩን የኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ገለጸ።
የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት በብሔራዊ ደረጃ የሚያገኙበት ሕጋዊና መሠረታዊ የመታወቂያ ዓይነት መሆኑ ይታወቃል።
የዲጂታል መታወቂያውም የዐይን፣የፊትና የጣት አሻራን ከግል መረጃ ጋር በማቀናጀት ኢትዮጵያውያን ያለአንዳች ከልካይ የሚያገኙት አገልግሎት ሆኗል።
የፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያም ዜጎች በከተማና በክልል ተቋማት የማይቀያየር፣ ዘመናዊና የታመነ አገልግሎት እንዲያገኙ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይሰጣል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም አስተባባሪ ዮዳሄ አርዓያሥላሴ፤ ዜጎችን የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ ምቹ የዲጂታል አገልግሎት ተደራሽነት ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በዚህም 24 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎችን የፋይዳ ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ማድረግ እንደተቻለ አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅትም 50 በመቶ ኢትዮጵያውያን የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ማድረግ የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህ በጀት ዓመትም የገጠሩ ማህበረሰብ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ እንዲያገኝ አስቻይ ሁኔታ የመፍጠር ስራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ሰባት ሺህ የሚሆኑ የምዝገባ ጣቢያዎችን ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን ተናግረዋል።
የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ በተለያየ ምክንያት ያላካሄዱ የማህበረሰብ ክፍሎች አሁንም በአቅራቢያቸው አገልግሎቱን እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።