ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአብሮነትን አቅም የተረዳንበት ትልቅ የኢኮኖሚ አውታር ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአብሮነትን አቅም የተረዳንበት ትልቅ የኢኮኖሚ አውታር ነው
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2017(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአብሮነትን አቅም የተረዳንበት ትልቅ የኢኮኖሚ አውታር ነው ሲሉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ ገለጹ።
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም እና ከፍታ በጋራ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያውያን ሕብረ ብሔራዊነት መገለጫ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጳጉሜን 4 ቀን 2017 በይፋ መርቀዋል።
ኢትዮጵያውያን በታላቁ ህዳሴ ግድብ ታሪክ ሰርተን ታሪክ ላይ ቆመን ለማውራት በቅተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ህዝቦች ታሪክ ሆኖ የሚኖር ነው ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት ዓባይ እግር እንጂ አፍ አልነበረውም፣ ለዚህም ኢትዮጵያውያን ሲያወሩለት ነበር ዛሬ ግን ዓባይ ራሱ ማውራት ጀምሯል በማለት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገር ልማት፣ በሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅም ላይ በጋራ መስራት እንደሚገባቸው እና እየሰሩም እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ምክር ቤቱም በዚህ ላይ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ በጋራ እንችላለን የሚል አቅም የተገነባበት ኢትዮጵያ ምን መስራት እንደምትችል ለዓለም ያሳየንበት ነው ብለዋል።
አብሮነት ትልቅ አቅም እንደሆነ ያየንበት ከፍተኛ የኢኮኖሚ አውታር መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያን ከድህነት እና ኋላቀርነት ታሪክ የሚያስወጣ ትልቅ አርማ ነው ብለዋል።
ሰብሳቢው ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅምና ከፍታ ላይ ፈጽሞ ልዩነት መኖር እንደሌለበት ገልጸዋል።
የኢዜማ ምክትል መሪ አርክቴክት ዮሃንስ መኮንን የሀሳብ ልዩነቶችን የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በማይጎዳ መልኩ ማስተናገድ ስልጡንነት መሆኑን ገልጸዋል።
የጋራ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሆኑን ገልጸው፤ ግድቡ የረጅም ጊዜ ቁጭትን በተግባር በመመለስ እውን ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቀቅ አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን በራስ አቅም መፍታት እንደሚችሉ ለዓለም ያሳዩበት የድል ብስራት መሆኑን አመላክተዋል።
ዘላቂ የሀገር ጥቅሞችን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ያለ ልዩነት አብሮ መቆም እና በዚህ ላይ የሚቃጡ ጥቃቶችንም ያለማንም አስተባባሪነት መመከት እንደሚገባ ጠቁመዋል።