የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለቱሪዝም ዘርፉ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል - የኢትዮጵያ ቱሪዝም እና ሆቴል ማህበር - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለቱሪዝም ዘርፉ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል - የኢትዮጵያ ቱሪዝም እና ሆቴል ማህበር
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2017(ኢዜአ)፦የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለቱሪዝም ዘርፉ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን የኢትዮጵያ ቱሪዝም እና ሆቴል ማህበር ፕሬዝደንት ጌታሁን አለሙ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያውያን ሕብረ ብሔራዊነት መገለጫ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጳጉሜን 4 ቀን 2017 በይፋ መርቀዋል።
ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በጉባ ተገኝተው ይህን ታሪክ፣ገድል፣ ማየት አለባቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህን የትውልድን ገድል ሁሉም መመልከት እንዳለበት መግለጻቸውም ይታወቃል።
ከለውጡ ወዲህ ለቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሶሶዎች መካከል አንዱ እንዲሆን መደረጉ ይታወቃል፡፡
ባለፉት ዓመታትም የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከማስፋት አኳያ በርካታ አዳዲስ መዳረሻዎችን ከማልማት ባሻገር ነባሮቹን የማደስ ስራዎች በስፋት ተከናውነዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቱሪዝም እና ሆቴል ማህበር ፕሬዝዳንት ጌታሁን አለሙ ለኢዜአ እንዳሉትም፥ህዳሴ በራስ አቅም የተሰራ የአሁኑ እና የመጭው ትውልድ ኩራት መሆኑን አንስተዋል፡፡
የግድቡ መጠናቀቅ በሆቴል እና ቱሪዝም እንዲሁም በባህር ላይ ትራንስፖርት የቱሪዝም አቅሙን በእጅጉ ያሳድጋልም ብለዋል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ እንደ ዓድዋ ድል ሁሉ የመላው አፍሪካውያን ኩራትና ተምሳሌት የሆነ ፕሮጀክት መሆኑን አንስተው፤ የኢትዮጵያዊያን ትብብር ውጤት በይፋ ያሳየ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በርካታ ፈተናዎችን አልፎ እውን የሆነ፤ የኢትዮጵያዊያን የአንድነት ውል ማሰሪያ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በታላቁ ህዳሴ ግድብ የተፈጠረውን የንጋት ኃይቅ ጨምሮ በርካታ ደሴቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ ለሚሰማሩ ምቹ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ጠቁመው፤ ይህም ለቱሪዝሙ ዕድገት መደላደል የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡