ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በድል መጠናቀቅ ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለማሳካት እንደምንችል ለዓለም ያሳየንበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በድል መጠናቀቅ ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለማሳካት እንደምንችል ለዓለም ያሳየንበት ነው
አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 5/2017 (ኢዜአ)፡-ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በድል መጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን ከዚህም በኋላ ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለማሳካት እንደምንችል ለዓለም ያሳየንበት ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።
ኢትዮጵያዊያን በህብር ሆነው በገንዘብ፣ የላብ እና የደም ጠብታ እውን የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ለምረቃ መብቃቱን አስመልክቶ ኢዜአ በአዲስ አበባ ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት ነው።
ግድቡ ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበት እንዲሁም መላ ኢትዮጵያዊያን አሻራቸውን ያስቀመጡበት እና ለፍፃሜው ያበቁት መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል ወይዘሮ ብሩክታዊት አሰበ እንዳሉት ከዚህ በፊት በአባይ ውሃ ለመጠቀም የህዝብ ቁጭት መኖሩን አስታውሰው አሁን ግን በራሳችን አቅም አሳክተነዋል ብለዋል።
አባይን በመገደብ ማንሰራራትን ለዓለም በተግባር አሳይተናል ያሉት ወይዘሮ ብሩክታዊት ስኬቱ ከዚህም በኋላ ሌሎች ፕሮጀክቶችን መስራት እንደምንችል ያረጋገጠ ነው ሲሉም ጠቁመዋል።
አባገዳ ሰቦቃ ለታ በበኩላቸው ከአስር ጊዜ በላይ የህዳሴ ግድብ ቦንድ መግዛታቸውን ገልጸው፤ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ርብርብ ተገንብቶ በመመረቁ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ አብነት አማኔ በበኩላቸው ከመቀነታችን ፈትተን ቦንድ ገዝተን ካለን ላይ በማዋጣት የገነባነው ግድብ በመጠናቀቁ በጣም ደስ ብሎኛል ብለዋል።
ለግድቡ ግንባታ በተለያየ መልኩ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን በመግለጽ፤ የዘመናት ቁጭት የነበረውን በህብረት አሳክተናል ሲሉም ጠቁመዋል።
አቶ ቶማስ ሻፊ በበኩላቸው እሳቸውም በተደጋጋሚ ከነልጆቻቸው ቦንድ ሲገዙ መቆየታቸውን ገልጸው፤ ህዳሴ የኢትዮጵያን ገጽታ የሚቀየር ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ስም የሚያድሰውን ግዙፍ ፕሮጀክት በጋራ በማሳካታችን ተደስቻለሁ ብለዋል።
ወይዘሮ ባንቺዓለም መንግስቱ በበኩላቸው ትውልዱ በጋራ በመሆን ያሳካው ግንባታ ለልጆቻችን ትልቅ በረከት ነው ብለዋል።