ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መመረቅ ከተባበርን የማናሳካው ነገር እንደሌለ አንዱ ማሳያ ነው-ወጣቶች

አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 5 /2017 (ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መመረቅ ከተባበርን የማናሳካው ነገር እንደሌለ አንዱ ማሳያና ለወደፊት ልማት ትልቅ ተስፋ የፈጠረ መሆኑን ወጣቶች ገለጹ። 

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ጥሩማር አባተ በበኩላቸው ወጣቶች ከአባቶታቻችን የተረከብነውን ባህሎች በመጠበቅ ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባናልም ብለዋል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም የገነቡትን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በይፋ መርቀዋል።

ወጣቶች የጎቤና ሽኖዬ ጨዋታን በማቅረብ በፕላንና ልማት ሚኒስቴር በመገኘት የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞት አስተላልፈዋል። 

በዚሁ ወቅት ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ወጣቶች እንዳሉት ከተባበርን የማናሳካው ነገር እንደሌለ የህዳሴ ግድብ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን ካለማንም ድጋፍ በራሳችን እውቀትና ሀብት የተገነባው ግድብ በመመረቁ በጣም ተደስተናል ሲሉም ተናግረዋል።


 

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወጣት ተስፋዬ አራርሳ እንደገለጸው፤ የህዳሴ ግድብ በድል መጠናቀቅ በተለይ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ላይ መሆኑ ለተሻለ ስራ የሚያነቃቃ ነው።

ሌላው ወጣት ዋጋሪ አበራ በበኩሉ ኢትዮጵያውን በጋራ ሆኖ ያሳኩት ግድብ ለሌሎች አገራት ተምሳሌት የሚሆን ነው።

በቀጣይ በህብረት በመስራት አገራችንን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር በአንድነት መስራት አለብን ብሏል።

ወጣት ገላና ሶቦቅሳ በበኩሉ ኢትዮጵያውን ከገንዘብ እስከ ህይወት መስዕዋትነት ከፍለው ለምረቃ መብቃቱ ከፍተኛ የድል ስሜት ይፈጥራል ብሏል።

ወጣት ብርሃኔ በየነ በበኩሏ የህዳሴ ግድብ መመረቁ የኤሌክትሪክ ኃይል ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች እንዲዳረስና ሁሉም ብርሃን እንዲያገኝ ያስችላል ብላለች።

ኢትዮጵያውያን ለተሻለ ድል እና ስኬት የበለጠ በመተባበር ሌሎች ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ማሳካት አለብን ብላለች።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ጥሩማር አባተ  ሁሉም ኢትዮጵያውያን በጋራ ሆነው ያሳኩት የህዳሴ ግድብ መመረቁ የኢትዮጵያውን የረጅም ጊዜ ልፋት ፍሬያፈራበት ነው ብለዋል።

ወጣቶች ጎቤና ሽኖዬ ጨዋታ በማቅረብ የእንኳን አደረሳችሁ ለማለት በመምጣታቸው እና ባህሉን በማሳየታቸው መደሰታቸውን ገልጸው፤ ከአባቶታቻችን የተረከብነውን ባህሎች በመጠበቅ ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባናልም ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም