በመዲናዋ ለመጪዎቹ በዓላት አስፈላጊውን የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችን ለመስጠት ዝግጅት ተጠናቋል - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ ለመጪዎቹ በዓላት አስፈላጊውን የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችን ለመስጠት ዝግጅት ተጠናቋል
አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 5 /2017 (ኢዜአ)፦በመስከረም 2018 ዓ.ም ለሚከበሩ በዓላት አስፈላጊውን የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችን ለመስጠት ዝግጅት መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ ጽህፈት ቤት ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት ጋር በመሆን በመስከረም 2018 ዓ.ም ለሚከበሩ ሃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላትን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በዚህ ወቅት የአዲስ አበባ ስራ አስኪያጅ ጽህፈት ቤት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ተፈራ ሞላ እንዳሉት፤ ከተማ አስተዳደሩ መጪ በዓላትን ለማክበር አስፈላጊውን አገልግሎት ለመስጠት በቂ ዝግጅት ተደርጓል።
ከከተማ እስከ ወረዳ ድረስ ግብረ ኃይል በማቋቋም በበዓላት ወቅት ቀልጣፋና አስተማማኝ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት መደረጉንም ነው ያስረዱት።
በዚህም መሰረት ለህብረተሰቡ አስተማማኝ የውሃ፣ ኤሌክትሪክ እና ሌሎች ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ተደራሽ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ ለሚያጋጥሙ ችግሮች መረጃ በመስጠት ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና ድንገተኛ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽነር ኮማንደር መሐመድ አህመድ በበኩላቸው፤ በዓላቱ አደጋ ሳይከሰት በሰላም እንዲያልፉ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።
አደጋን ቀድሞ ለመከላከል ህብረተሰቡን የማስገንዘብ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ ህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ መገልገያዎችንና ከሰል ሲጠቀም ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ መክረዋል።
የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሞገስ አርጋው፤ በበዓላቱ ወቅት በቂ የውሃ አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል።
ህብረተሰቡ ከውሃና ፍሳሽ ጋር የተያያዘ ማንኛውም ችግር ቢገጥመው በ906 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ ማቅረብ እንደሚችልም ተናግረዋል።
በበዓላቱ ወቅት ለህብረተሰቡ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ዝግጅት ተደርጓል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዲስ አበባ ሪጅን ማስተባበሪያ ቢሮ ምክትል ስራ አስፈፃሚ ጂሳ ካሳ ናቸው።
የመብራት አገልግሎት አስተዳደር ባለስልጣን ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ጁናይድ ከማል በበኩላቸው፤ ህብረተሰቡ በዓላትን በሚያከብርበት ወቅት መሰረተ ልማቶች እንዳይጎዱ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።